ነሀሴ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እየተካሄደ ባለው የለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያዊቷ ሶፊያ አሰፋ በ3000 ሜትር የሴቶች መሰናክል የነሀስ ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን፦ የመንፈስ አባቷን የአትሌት እሸቱ ቱራን ድል ደግማለች።
አትሌት እሸቱ ቱራ በ1980 በተካሄደው የሞስኮ ኦሎምፒክ በ 3000 መሰናክል የነሀስ ሜዳሊያ አሸናፊ በመሆን፤ በኦሎምፒክ የመሰናክል ውድድር ለራሱና ለአገሩ የመጀመሪያ የሆነውን አንጸባራቂ ድል መቀዳጀቱ ይታወሳል።
ቆፍጣናዋ ጀፍና ሶፊያ አሰፋ ከ 33 ዓመት በሁዋላ ነው ይህን ድንቅ ታሪክ የደገመችው።
ሶፊያ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 9 ደቂቃ 9 .84 ሰከንድ ነው።
ውድድሩን በ 6 ደቂቃ 72 ሰከንድ በአንደኝነት ያጠናቀቀችው የሩሲያዋ ዩሊያ ዛሪፖቫ ስትሆን፤እሷን ተከትላ በ 9 ደቂቃ 8 .37 ሰከንድ የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው ደግሞ የቱኒዚያዋ ሀቢባ ግሪቢ ናት።
ለረዥም ጊዜ በመሰናክል ሩጫ ባለድሎች የነበሩት ኬንያውያው፤ በዚህ የሴቶች መሰናክል ውድድር ውጤት ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
አትሌት እሸቱ ቱራ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ውስጥ የመሰናክል ሩጫ አሰልጣኝ ነው።
በሌላ በኩል ዛሬ ማርፈጃውን በለንደን ኦሎምፒክ ስታዲየም በተካሄደው የ5000 ሜትር የሴቶች ማጣሪያ ጠያይሞቹ ፈርጦች ጥሩነሽ ዲባባ እና መሠረት ደፋር አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ወደ ፍጻሜው ፍልሚያ አልፈዋል።
አትሌቶቹ በማጣሪያው ያሳዩት ብቃት እና በራስ መተማመመን ኢትዮጵያ በርቀቱ ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን እንደምታገኝ ከፍ ያለ ግምት አሳድሯል።
____________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide