ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ ይቅርታ አልጠይቅም አሉ

ሐምሌ ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባለቤታቸው የታሰሩባቸው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ፦”ይቅርታ ጠይቁ” በመባላቸውን በመጥቀስ፦” የሠራሁት ስህተት ስለሌለ የምጠይቀው ይቅርታ የለም” አሉ።

ባለቤቴ  ከህፃናት ልጆች ተነጥላ ትክክለኛ ባልሆነ ማስረጃ ታስራብኛለች ሲሉም  አቤት አሉ።

ሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ  የባለቤታቸውን መታሰር አስመልክቶ በኢትዮ ቻነል እና በሰንደቅ ጋዜጦች ለወጡት ዜናዎች መልስ በሰጡበትና በዛሬው የ ኢትዮ ቻነል ጋዜጣ ላይ በታተመው ጽሁፋቸው  ፤በጋዜጦቹ የወጡትን ጽሁፎች ተከትሎ  ባለቤታቸው  ከሰሞኑ የ እስልምና ተከታዮች እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተደርጎ የሚወራው ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል።

ባለፈው ሐምሌ 9 ቀን ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ገደማ ባለቤታቸው ከሳዑዲ ኤምባሲ ሲወጡ በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸው እውነት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጁነዲን፤ እርሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ከሳዑዲ አምባሳደር ጋር ያላቸው ግንኙነት ከ አንድ ዓመት ተኩል እንደማይበልጥና ከሰሞኑ እንቅስቃሴ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ጠቁመዋል።

አቶ ጁነዲን በጽሁፋቸው እንዳሉት በግንቦት ወር 2001 ዓመተ ምህረት እናታቸው ከዚህ ዓለም በሞት  ሲለዩ፤ መኖሪያቸው በሆነው በ አርሲ ዞን ሎዴ-ሄጦሳ ወረዳ ሼመቻ ቤጎ ውስጥ በሚገኘው ቦታቸው ላይ መስጊድ ሠርተው ጸሎት እንዲያደርጉላቸው ይናዘዛሉ።

ይህንም የ አደራ ቃል ለመፈጸም  በ አካባቢው የሚገኙ ሰዎችን በማስተባበር እንቅስቃሴ መጀመሩን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ሆኖም በቂ ገንዘብ ሊገኝ ባለመቻሉ ሥራው በጅምር መቆሙን አትተዋል።

የመስጊዱ ሥራ ለ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ሲቆምም፤የዚህ ዓይነት በጎ ድጋፎችን ያደርጋሉ የሚባሉት የሳዑዲ አምባሳደር እርዳታ እንዲያደርጉልን ራሴ ጠየቅኳቸው ብለዋል-አቶ ጁነዲን።

ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ የገንዘብ እርዳታ እንደተፈቀደላቸው ያመለከቱት ሚኒስትሩ፤ ገንዘቡ ኤምባሲው በወከለው አንድ ሰው  አማካይነት ወጪ እየተደረገ ለባለቤታቸው  እንደሚሰጥና ባለቤታቸውም ገንዘቡን በመቀበል ሥራውን እንደሚያስፈፅሙ ገልጸዋል።

ባለቤታቸው ወይዘሮ ሀቢባ ከሳምንታት በፊት በፖሊስ የተያዙትም ለመስጊዱ ማስፈጸሚያ የሚሆንን እና በዚህ መልክ የተለቀቀን 50 ሺህ ብር ይዘው ሲወጡ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በጋዜጦቹ  ከዚህ ከፍ ያለ ገንዘብ እንደያዘች ተደርጎ የተዘገበው ስህተት እንደሆነ አመልክተዋል።

በመኪና ላይ ተገኘ የተባለውም ዕቃ ሰደቃ ሊደረግበት ነው የተባለው ስህተት እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ጁነዲን፤ የልዩ ጥበቃ ፖሊስ ዘወትር ከባለቤቴ ጋር በ አጃቢነት እየተንቀሳቀሰ እንዴት እንዴት እኩይ ተግባር ይሠራል ተብሎ ተጠረጠረ? ሲሉ ጠይቀዋል።

“የፖሊስ ጥርጥሬ ባለቤቴ ከ ሳ ዑዲ ኤምባሲ  በተደጋጋሚ ገንዘብና የቅስቀሳ ወረቀት እየተቀበለች ለግርግርና ረብሻ ፈጣሪዎች ትሰጣለች የሚል እንደሆነ ተደርተናል” ብለዋል ሚኒስትሩ።

አያይዘውም ባለቤታቸው ፈጽሞ ይህን ሊያደርጉ የማይችሉ ሴት መሆናቸውን ባህርያቸውን በመዘርዘር ሊገልጿቸው ሞክረዋል፦

“ባለቤቴ እጅግ በጣም ንጹህ የቤት እመቤት፣እንኳንስ ከሚያከሩ ሀይሎች  ግንኙነት ሊኖራት ቀርቶ የረባ ጓደኛ የሌላት፣ሙሉ ጌዜዋን ልጆቻችንን በማስጠናት እና ቤታችንን በማቃናት ላይ የተሠማራች፣ ቁጥብና ጨዋ ሴት ናት” በማለት።

በመሆኑም ከሰሞኑ እንቅስቃሴ ጋር ፍጹም ግንኙነት እንደሌላለቸው፤ይልቁንም እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አጥብቀው እንደሚቃወሙ በተደጋጋሚ አበክረው የገለፁት አቶ ጁነዲን፤ሀቁ ይህ በሆነበት ሁኔታ ባለቤታቸው ባልተሟላና በተሣሳተ መረጃ መታሰራቸው ቅር እንዳሰኛቸው ገልጸዋል።

“ባለቤቴ ከህፃናት ልጆች ተነጥላ መታሠሯ፤በቤተሰቤና በኔም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ፖሊስ ለጠረጠረበት ወንጀል እስካሁን ያገኘው አንድም ማስረጃ የለም ብለዋል።

“ስለዚህ ባልሆነ አቅጣጫ የተወረወረው ቅዝምዝም ወደ አቅጣጫው ይመለስ።የሠራነው   የሙት እናት ቃል ለማሳካት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም።እንደ ሚኒስትርነቴ ሳይሆን እንደ ግለሰብ  በሌጣ ደብዳቤ የጠየቅኩት ዕርዳታ መሆኑ ይታወቅልኝ”ብለዋል።

“ይቅርታ ይጠይቅ የተባለውም፤ሙሉ በሙሉ ስህተት ስለሆነ  የምጠይቀው ይቅርታ አይኖርም” ያሉት አቶ ጁነዲን፤በመንግስት ጉያ ውስጥ ሆኜ መንግስትን የሚጎዳ ሥራ ሠርቼ አላውቅም” ብለዋል።

የሚኒስትሩን ደብዳቤ  ያነበቡ ወገኖች፤ ነገሩ፦የኦህዴዱ አቶ ጁነዲን ሳዶ የሲቪል ሰርቪሰ ሚኒስትር  የሚል ትልቅ ሹመት የተለጠፈላቸው ለይስሙላ መሆኑን እና ከህወሀቶች ውጪ በዚች አገር መብትና ትክክለኛ ሥልጣን ያለው ሰው የሌለ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል የፍትህ ሚኒስትር የነበሩት የደቡቡ  አቶ አሰፋ ከሲቶ  ያለተለዋጭ ቤት  ከተከራዩበት ቤት በሀይል  እንዲወጡ መደረጉ፣ ዕቃቸው ሜዳ ላይ በፖሊሶች  መበታተኑ እና   ከባለቤታቸውና ከህፃናት ልጆቻቸው ጋር ሜዳ ላይ መውደቃቸው ይታወሳል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide