የሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ታሰሩ

ሐምሌ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ የ አቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ከሳዑዲ ዓረቢያ የሃይማኖት አታሼ ቢሮ ገንዘብ ይዘው ሲወጡ ተይዘው መታሰራቸውን ሰንደቅ ጋዜጣ ዘገበ።

ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሃቢባ መሐመድ መሐሙድ ፤በወረዳ 17 ወርቁ ሕንፃ አጠገብ ከሚገኘው ከሳዑዲ ዓረቢያ የሃይማኖት አታሼ ቢሮ ግምቱ ከሃምሳ እስከ መቶ ሺ ብር የሚገመት የታሰረ ገንዘብ እና በዓረብኛ የተፃፉ መፅሐፍት ይዘው ሲወጡ በፌዴራል ፖሊስ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

ወይዘሮ ሃቢባ መሐመድ  እጅ ከፍን ጅ ተይዘው  በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ ትናንት ሐምሌ 10 ቀን 2004 ዓ.ም በሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ ውስጥ የሃይማኖት አታሼ ኃላፊ ከሆኑት ፋህድል ቃህታኒ ቢሮ ውስጥ ከቀኑ ከ8፡30 እስከ 9፡30 ሰዓት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ቆይታ አድርገው ሲወጡ  ነው።
ወይዘሮ ሃቢባ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያው የሃይማኖት አታሼ ቅጥር ግቢ ውስጥ የገቡትም፤የሰሌዳ ቁጥሩ 65602 በሆነ  የመንግስት ነጭ ኮብራ መኪና  ሲሆን፤ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፖሊስ በዚሁ ላንድክሩዘር መኪና ውስጥ ባካሄደው ፍተሻ በአራት ካርቶን ውስጥ በቁጥር አምስት መቶ የሚሆኑ በዓረብኛ ቋንቋ የተፃፉ መፃሐፍት ተገኝተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ የማብሰያ መሣሪያዎች ከላንድክሩዘሩ መቀመጫ በስተጀርባ ላይ ተጭነው መገኘታቸውን የጋዜጣው ምንጮች ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሃቢባ ወደ ሳዑዲው የሀይማኖት አታሼ ቢሮ ሲገቡ፤ አንድ የአቶ ጁነዲን ሳዶ የግል ጠባቂና ሹፌራቸው አብሯቸው እንደነበሩ ምንጮቹ ጨምረው ጠቁመዋል።
ጋዜጣው፦“ ወይዘሮ ሀቢባ የተያዙት የመንግስት ንብረት በሆነ ተሽከርካሪ ወደ ሚስተር ፋህድል ቢሮ ስለገቡ ነው? ወይንስ ከኤምባሲው የሃይማኖት አታሼ ኃላፊ  ጋር  የተለየ ግንኙነት ፈጥረዋል በሚል ነው? ወይንስ የተለየ ተልዕኮ ሊኖራቸው ይችላል ከሚል ስጋት ነው?” በማለት ጥያቄ ያቀረበላቸው አንድ የማዕከላዊ ፖሊስ ሀላፊ፤  የወይዘሮ ሃቢባ መሐመድን መታሰር አምነው፤ ሆኖም ግን ጉዳዩ በምርመራ ላይ ያለ በመሆኑ ዝርዝር መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide