ግንቦት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሰሞኑን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር ያደረገውን የ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመደገፍ ወደ ስታዲየም የገቡ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የአቶ መለስ መንግስትን አጠንክረው መቃወማቸው ተዘገበ።
በሺዎች የሚቆጠሩ በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በጨዋታው ቦታ ተገኝተው ብሔራዊ ቡድናቸውን ለመደገፍ ወደ ደቡብ አፍሪካ-ሮያል ቦፎኬንግ ስታዲየም የተመሙት አረንጓዴ፣ቢጫና ቀይ ባንዲራቸውን እያውለበለቡ ነበር።
ተቃውሞው የተጀመረው ልክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር መዘመር ሲጀምር መሆኑ ታውቋል።
ባፋና ባፋናዎች የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ መዝሙርን ከህዝባቸው ጋር ዘምረው ካጠናቀቁ በሁዋላ- በቀጣይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር እንደሚሰማ የስታዲየሙ መርሀ-ግብር መሪ ያስተዋውቃል።
ከዚያም፦”የዜግነት ክብር…”በሚል ሀረግ የሚጀምረው የዘመነ-ኢህአዴግ መዝሙር እንደተጀመረ በስፍራው የተገኙት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ አንድ ላይ ፦”ኢትዮጵያ፤ የኛ መመኪያ…”በሚለው የጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ ስታዲየሙን አደበላልቀውታል።
ኢትጵያውያኑ በአንድ ድምጽ የሚያሰሙት ሙዚቃ በሜዳው ሙሉ አይሎ በማስተጋባቱ የብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች ፦”የዜግነት ክብር…” የሚለውን መዝሙር ለመዘመር ግር ብሏቸው ታይተዋል።
በዚህ የተጀመረው ተቃውሞ በብሔራዊ ቡድናችን የመጀመሪያ ጎል ተሟሙቆ ኢትዮጵያውያኑ የአቶ መለስን መንግስት አጠንክረው ሲቃውሙ አምሽተዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገርን ነፃ ለማውጣት እየተደረገ ባለው ትግል እያሳዩት ያለው ጠንካራና የትብብር ተሳትፎ በሌሎች አገሮች በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍ ያለ መነጋገሪያ እየሆነ ነው።
ኢትዮጵያውያኑ በተለይ በቅርቡ ወደ ጆሀንስበርግ ላቀኑት ለአርቲስ ታማኝ በየነ፣ለአርቲስት ሻምበል በላይነህ እና ለጋዜጠኛ ገሊላ መኮንን ያደረጉት ደማቅ አቀባበል እና በተሳካ ሁኔታ ያካሄዱት የ ኢሳት ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የብዙዎችን ልብ የነካ ሆኗል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide