ግንቦት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በጋምቤላ የተሰማሩ ባለሀብቶች በህይወታቸው ዋስትና ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ እና ከግብርና ሚኒስትሩ ጋር ተነጋገሩ።
በጋምቤላ ክልል በተፈጸሙ ተመሣሳይና ድንገተኛ ጥቃቶች አንዳንድ ባለሀብቶች ሥራቸውን እርግፍ አድርገው በመተው ከክልሉ ለመውጣት ሲወስኑ፤ በሥራቸው ለመቀጠል ፈልገው ከፍ ያለ ድንጋጤና ፍርሀት ውስጥ የገቡ ባለሀብቶች ደግሞ የህይወታቸውን ደህንነት በተመለከተ መንግስት ዋስትና እንዲሰጣቸው ሰሞኑን ጥያቄ አቅርበዋል።
ባለሀብቶቹ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ለአለቃ ፀጋይ በርሄ እና ለግብርና ሚኒስትሩ ለአቶ ተፈራ ደርበው ነው።
በዚሁ መድረክ ላይ ባለሀብቶቹ ፦”በተለይ በቅርቡ በአንድ እርሻ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከፈጠረብን ድንጋጤ አልተላቀቅንም”ሲሉ ተደምጠዋል።
የባለሀብቶቹን ስጋት እና ጭንቀት ያዳመጡትም ባለሥልጣናት፤ ሥራቸውን ተረጋግተው እንዲሠሩ መክረዋል።
ይሁንና ተረጋግተው እንዲሠሩ ምክር ከማስተላለፍ ውጪ በተጨባጭ ደህንነታቸውን በተመለከተ መንግስት ስለሚያደርግላቸው ጥበቃ በዝርዝር የተገለጸ ነገር የለም።
በሌላ ዜና ከአራት ሺህ የሚበልጡ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ጋምቤላ ገብተዋል።
የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር እንደገለፀው፤ ወደ ጋምቤላ የገቡት ስደተኞች ከደቡብ ሱዳን-የጆንግሌይ ግዛት አኮቦ በተባለ አካባቢ ባለፈው ጥር ወር በተፈጠረ የጎሳ ግጭት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ናቸው።
አዲስ ዘመን እንዳለው፤ ስደተኞቹ ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ በጋምቤላ ክልል በሚገኘው ፉኝዶ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ማረፋቸው ተመልክቷል።
በጋምቤላ ክልል በሦስት የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መካከል ከ 30 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጋር በመተባበር ወደ አገራቸው እንደመለሰ የገለፀው የ ኢትዮጵያ መንግስት፤አዳዲሶቹን ጨምሮ በ አሁኑ ጊዜ ከ 26 ሺህ የሚበልጡ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በፑኝዶ የስደተኞች መጠለያ እንደሚገኙ አመልክቷል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide