በአቧሬ- አድዋ አደባባይ ፊት ለፊት ተሰቅሎ የነበረው የአቶ መለስ ግዙፍ ምስል ባልታወቁ ሰዎች መሰረቁ ተዘገበ

ግንቦት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፍኖተ -ነፃነት እንደዘገበው፤በኢሳያስ ማስታወቂያ ታትሞ ከአምስት ቀናት በፊት አድዋ አደባባይ ላይ ተሰቅሎ የነበረው ይኸው የአቶ መለስ ምስል፦ “በዘመነ ትውልድ ያልተደፈረውን አባይ የደፈረ ጀግና” የሚል መፈክር የያዘ እንደነበር የድርጅቱ ባለንብረት ለጋዜጣው  ተናግሯል፡፡

ሁኔታውን እንቆቅልሽ ያደረገውም፤የአቶ መለስ ግዙፍ ምስል የተሰረቀው በቀን መሆኑ ነው ተብሏል ።

በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር ወጪ የሆነባቸው የአቶ መለስን ተክለ ስብዕና የሚገነቡ ምስሎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች  በየቢል ቦርዶች ላይ  በብዛት እየተሰቀሉና በቁልፍ መያዣዎች ላይ ታትመው እየተሰራጩ ይገኛሉ።

ይሁንና በአቶ መለስ ምስል ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጥፋት፣የመነሳት ወይም የመሰወር አደጋ ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው ጊዜ መሆኑ፤ዜናውን በብዙ አቅጣጫ አነጋጋሪ አድርጎታል።

ከአምስት ቀናት በፊት በአድዋ አደባባይ  ተሰቅሎ  ለተሰረቀው  ለዚህ የአቶ መለስ ምስል የፍሬም ሥራውን ጨምሮ  ከ35,000 (ሰላሣ አምስት ሺህ) ብር በላይ ማውጣቱን አቶ ኢሳያስ ተናግሯል ፡፡

አቶ ኢሳያስ ፤  7 ሜትር በ 4 ሜትር የሆነውና 28 ካሬ ስፋት ያለው ይህ ግዙፍ ምስል በጠራራ ጸሀይ  በመጥፋቱ መደንገጡንም ገልጿል፡፡

እስካሁን ማረጋገጥ የቻለው፤በዘመናዊ ዲጂታል የህትመት መሣሪያ በኢሣያስ ማስታወቂያ ታትሞ በአቧሬ አድዋ አደባባይ ፊት ለፊት ተሰቅሎ የነበረው  የአቶ መለስ ምስል ተገንጥሎ  መወሰዱን ብቻ ነው፡፡

ድርጊቱን፤ የማስታወቂያ ባለቤቱን ጨምሮ አንዳንድ  የአካባቢው ነዋሪዎች ከዝርፊያ ጋር ሢያመሣስሉት፤አንዳንዶች ግን፤ “ማን ገንጥሎ ወሰደው?ለምንስ ጉዳይ ወሰደው?” የሚለው  ጥያቄ ከዚህም በላይ የሚያጠያይቅና የሚያነጋግር ነው ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፊት ፤በመገንባት ላይ ያለው ህዳሴው ግድብ ከሁዋላ ሆነው  ከሚታዩበት ከዚህ ግዙፍ ምስል  ሥር  በትልቁ፦ “በዘመነ ትውልድ ያልተደፈረውን አባይ የደፈረ ጀግና” የሚል መፈክር ተጽፎበት ነበር።

አቶ አርከበ ዕቁባይ  የአዲስ አበባ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የ ኤች.አይ.ቪ /ኤድስ ምርመራ በይፋ በማድጋቸው  የተደሰተ አንድ  ከኤች.አይ.ቪ ጋር የተያያዘ ሥራ የሚሰራ የማስታወቂያ ድርጅት ፤ የደም ምርመራ ሢሰጡ የሚያሳየውን ምስላቸውን በትልቁ በማድረግ ፒያሳ ከማዘጋጃ ፊት ለፊት ቢሰቅለውም፤ ከጥቂት ቀናት በሁዋላ በህወሀት ውሳኔ እንዲነሳ መደረጉ ይታወሳል።

ህወሀት ለአቶ አርከበ ምስል መነሳት ያስቀመጠው ምክንያት፤ አንድን ግለሰብ ነጥሎ ማውጣት፦ ድርጅቱ ከሚከተለው ከብዙሀዊነት መስመር ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ነው የሚል እንደነበር የድርጅቱ አባላት በጊዜው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የአቶ አርከበ ምስል ከተነሳ በሁዋላ  በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ፦”እርስዎ  የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራ አድርገዋል ወይ?”ተብለው የተጠየቁት አቶ መለስ፦”እንደ ሌሎቹ ለገበያ አላወጣሁትም እንጂ፤ተመርምሬያለሁ”በማለት አቶ አርከበን በአደባባይ ሸነቆጧቸው።

ይሁንና   “ተመርምረን ራሳችንን እንወቅ”በሚል መርህ ሲካሄድ ለነበረው የፀረ-ኤች አይ ቪ ዘመቻ  አቶ አርከበ በይፋ የተመረመሩ የመጀመሪያዊ ባለስልጣን በመሆናቸው ሳቢያ በአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት  ምስላቸው መሰቀሉ ፦”ከገበያ መውጣት”ጋር ተያይዞ እንዲነሳ በተደረገ ማግስት፤ የአቶ መለስ ምስሎች እንደ ዓፄ ሀይለሥላሴ እና እንደ ኮሎኔል መንግስቱ በአንዳንድ መፃህፍት መግቢያ ገፆች ላይ እየታተሙ መታዬት ጀመሩ።

የአቶ መለስ ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው፤  በአቶ በረከት ስምዖን  የሚመራው ማስታወቂያ ሚኒስቴር  በየስድስት ወሩ በሚያሳትመውና በየድርጅቶችና መስሪያ ቤቶች በሚሰራጨው “አገርህን ዕወቅ” የሚል መጽሐፍ መግቢያ ገፅ ላይ ነው።

ከዚያም በአንዳንድ የመማሪያ መፃህፍት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስሎች  ታዩ።  ከምርጫ 97 በሁዋላ ደግሞ አቶ መለስ በየቢል ቦርዶች እና በየቁልፍ መያዣዎች ላይ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ።

በተለይ ከአራት ዓመታት በፊት የተከበረውን የኢትዮጵያ ሚሊኒየም አስመልክቶ በብዙ ሚሊዮን ብር የታተሙ የአቶ መለስ ምስሎችና የአቶ መለስን ምስል የያዙ ቁልፍ መያዣዎች  ተሰራጩ። ግዙፍ ቢል ቦርዶችም በየከተሞች መግቢያ እና  በየጎዳናዎች ላይ ተሰቀሉ።

በህወሀት፣  በኢህአዴግ ሆነ በመንግስት መዋቅር  ውስጥ አቶ መለስ ብቸኛ አድራጊ ፈጣሪ ሰው ሆነው የወጡት፤ ህወሀት ለሁለት ተከፍሎ የነ ስዬ ቡድን ከተገለለ በሁዋላ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

የአቶ መለስን ብቸኛ አድራጊ ፈጣሪነት የተገነዘቡ የቀድሞ የድርጅቱ አባላት፦ “የድርጅቱ የብዙሀዊነት መስመር አንድን ሰው በማንገስ ተቀይሯል፤ ብዙሀኑ የኢህአዴግ አባላትም ዙፋን ተሸካሚነትን መርጠዋል” ሲሉ ይደመጣሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide