ግንቦት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጽያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰማያዊ ፓርቲ በሚል ሰያሜ ሕጋዊ ሰውነት እንዳገኘ አድርጎ የሚጠራው አካል ሕጋዊ ሰውነት አለማግኘቱን በመግለጽ ወሬውን የሚዘግቡ ፕሬሶችንና ፓርቲውን ከአድራጎታቸው እንዲቆጠቡ ሲል አሰጠነቀቀ፡፡
በቦርዱ ጽ/ቤት ምክትል ዋና ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ አሰፋ ፊርማ ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ የተሰራጨው መግለጫ እንደሚያትተው ሰማያዊ ፓርቲ ቦርዱ እንዲያሟላ የጠየቀውን ሰነዶች ያላሟላ በመሆኑ ሕጋዊ ሰውነት አልተሰጠውም፡፡በመሆኑም ፓርቲው ከአድራጎቱ እንዲቆጠብ፣ሕጋዊ ዕውቅና ያላገኘ ፓርቲን ሕጋዊ እንደሆነና ዕውቅና እንዳገኘ በማስመሰል ለሕዝብ ማቅረብ ለሕዝባችን እና ለአገራችን እንደማይበጅ በመገንዘብ ሚዲያዎቹ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲል አስጠንቅቋል፡፡
የቦርዱ መግለጫ ሰማያዊ ፓርቲን በተመለከተ የተፈጠረውን ችግርም ዘርዝሮ ያስረዳል፡፡“እነዚህ ወገኖች በአዋጁ ማሟላት የሚገባቸውን ሁሉ አሟልተናል ብለው ሰነዶቻቸውን አቅርበዋል፡፡ጽ/ቤቱም የቀረበውን ሰነድ መሟላት፣አለመሟላቱን አጣርቶ በመለየት ለቦርዱ ውሣኔ አቅርቧል፡፡ቦርዱም ከጽ/ቤቱ ተጣርቶ የቀረበለትን በጥልቀት መርምሮ ያልተሟሉ ጉዳዮች ተሟልተው እንዲቀርቡ ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡በዚሁ መሠረት ለመጀመሪያ ግዜ 22፣ለሁለተኛ ግዜ አራት ያልተሟሉ ጉዳዮች እንዲሟሉ በደብዳቤ ተዘርዝሮ እንደተገለጸላቸው ያትታል፡፡ፓርቲው ለሶስተኛ ግዜ ያቀረበው ሰነድ ሲመረመር ሁለት ያልተሟሉ ጉዳዮች እንዳሉ በመረጋገጡ ይህንን አሟልተው እንዲያቀርቡ እንደተነገራቸው መግለጫው ይጠቅሳል፡፡እነዚህ ጉዳዮችንም ምን እንደሆኑ ጠቅሷል፡፡
በቦርዱ አልተሟሉም የተባሉ የአዋጁ ድንጋጌዎች፡-
1….በአዋጁ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 2/ሠ መሰረት መሥራቾች የፈረሙበት ለሕዝብ ይፋ የሆነ ሰነድ አለመሟላት፣
2….በአዋጁ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 1/መ መሰረት የሃብትና የንብረት ፣የገቢና የወጪ ሰነዶች ተሟልተው አልቀረበም የሚል ነው፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የመሥራች አባላት ፊርማ ለሕዝብ ይፋ መሆንን በተመለከተ ቦርዱ መመሪያ እንደሚያወጣ በአዋጁ የተደነገገ ቢሆንም እስካሁን የወጣ መመሪያ ባለመኖሩ ፊርማው በምን መልክ፣በማን፣የት ይፋ እንደሚሆን የሚታወቅ ነገር ባለመኖሩ ይህን ለማሟላት መቸገራቸውን፣ጥፋቱም የእነሱ እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ ቦርዱ በበኩሉ እስከዛሬ የሚሰራበትን መንገድ
እንደተነገራቸው ገልጻል፡፡ቦርዱ ግን እነዚህ ጉዳዮች እንዲሟሉ ለአራተኛ ግዜ ደብዳቤ ቢጽፍላቸውም ደብዳቤውን በጽ/ቤት ተገኝተው ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም ብሏል፡፡
በኢንጅነር ይልቃል ጌታሁን የሚመራውና በሙህራን ወጣቶች የተገነባው ሰማያዊ ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ ጋር የገጠመውን ችግር አስመልክቶ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ከጥር 14 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ የእውቅና ጥያቄውን ለቦርዱ ያቀረበ ቢሆንም ቦርዱ አላሰፈላጊ ጥያቄዎችን እያነሳ ከሶስት ወራት በላይ እውቅናውን በማዘግየቱ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 9 ንዑስቁጥር 5 እና 7 በሚደነግገው መሰረት ማለትም ቦርዱ የቀረበለትን የማመልከቻ አባሪ ሰነድ በተቀበለ በሶስት ወራት ግዜ ውስጥ የምዝገባ ፎርማሊቲውን አጠናቆ ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለአመልካቹ እንደሚሰጥ ነገር ግን በተጠቀሰው ግዜ ውስጥ ምላሸ ካልሰጠ የምዝገባ ማመልከቻ ያቀረበውን ፓርቲ እንደተመዘገበ ይቆጠራል ይላል፡፡በዚህ ድንጋጌ መሠረት ሰማያዊ ፓርቲ ከሚያዝያ 13 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ህጋዊ መሆኑን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡
ቦርዱ ግን ፓርቲውን እና የፓርቲውን ድምጽ እያሰሙ ያሉ በተለይ የግሉን ፕሬስ በዛሬ መግለጫው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲል አስጠንቅቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የጠየቅናቸው የፓርቲው አንድ አመራር አባል ፓርቲው ሕጋዊ አካሄድን ተከትሎ እየተጓዘ መሆኑን፣ሕግን አላከብርም ያለው ቦርዱ መሆኑን በመጥቀስ ሰማያዊ ፓርቲ ሕጋዊ መብቱን ፍ/ቤት ጭምር ለማረጋገጥ ወደኃላ እንደማይል ጠቁመዋል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide