የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ከዚህ በላይ ልንታገሰው አንችልም ሲሉ ሚኒስትሩ ተናገሩ

ሚያዚያ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-የፌዴራል ጉዳዮች ሚ/ር  የሆኑት ዶ/ር ሺፈራው ተ/ማርያም ሙስሊሙ ኀብረተሰብ በሰላም እንዳይጸልይ ያውካሉ ያሏቸውን ጸረ ሠላም ኃይሎች መንግስት ሊታገሰቻው በማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ነው የገለጡት፡፡

ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት የመ/ቤታቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት በአሁኑ ግዜ በየመስጊዱ ህዝበ ሙስሊም የአርብ ጸሎትን በሰላም እንዳይጸልይ በማወክ በግልጽና በህቡዕ የሚንቀሳቀሱና ሰላምን ፣ልማትን የሚያውኩትን ጸረ ሰላም አክራሪ ኃይሎች ሕዝቡ እንዲመክራቸው፣እንዲገስጻቸው ጠይቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ በዚሁ ሪፖርታቸው“ ጸረ ሰላም ”ያሏቸውን ኃይሎች ከዚህ በላይ መታገስ እንደማይቻልም ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ሺፈራው ከቅርብ ግዜ ወዲህ በእስልምና ሃይማኖት ሸፋን የሚንቀሳቀሱ ጥቂት አክራሪ ኃይሎች ሕዝበ ሙሲሊሙን በማደናገር ፣በመደለል በማሰፈራራት፣እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ከመናገር አልፈው አክራሪ ያሏቸው ኃይሎች አንዳንድ ጋዜጦችን፣መጽሔቶችን፣የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ዘዴዎችን ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ እየተጠቀሙ ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡

መንግስት ለሕዝበ ሙስሊሙ ባለው ከበሬታ በአውሊያና በእሥልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት ጉዳይ ጥያቄ አለን ብለው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ግለሰቦች ጋር ሲወያይ እንደነበር አስታውሰው መንግስት ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እያለ ከጀርባቸው ያሉ የትርምስ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሙስሊሙን  ማደናገሩን ተያይዘውታል ብለዋል፡፡መንግስት ነገሩን በእርጋታ መያዙ በእነዚህ ኃይላት እንደፍራቻ ተቆጥሯል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

 በም/ቤቱ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጭ የሆኑት አቶ ግርማ ሠይፉ በሰጡት አስተያየት በተለይ በጅምላ ሕዝበ ሙስሊሙ የሚደናገር፣የሚደለል ሆኖ በሚኒስትሩ መቅረቡ ተገቢ እንዳልሆነ በመጥቀስ “ሕዝብ የመሳሳት ሳይቀር መብት እንዳለው ልታውቁ ይገባል፡፡ሕዝብ የተሳሳተ ውሳኔ የማሳለፍ መብት፣የተሳሳተ  ፓርቲ የመምረጥ መብት አለው፣መሳሳቱን ባወቀ ግዜም የቀድሞ ስህተቱን

የማረም፣መልሶ ያለመምረጥ መብት አለው፣ምርጫም  የሚያስፈልገው ለዚህ ነው” ብለዋል

 በሌላ በኩል ደግሞ ከብዙሀኑ ሙስሊም አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተበተነ በተባለ ወረቀት ላይ፤ የመጂሊስ አመራሮች ሙሉ በሙሉ እንዲወርዱ ውሳኔ መተላለፉ ታውቋል።

ውሳኔውን በማን እና በምን መልኩ እንደተላለፈ በወረቀቱ ላይ የተገለፀ ነገር የለም።

አስተባባሪዎቹ ለብዙሀኑ ሙስሊም በተኑት በተባለው  ወረቀት፤፦”ሁላችንም ነገሩን በጥንቃቄ እና በንቃት መከታተል አለብን። የመጂሊስ አመራሮች ሙሉ በሙሉ እንዲወርዱ ተወሰነ ተባለ እንጂ ወርደዋል አልተባለም።አመራሮቹ አሁንም ገና ቦታቸው ላይ ናቸው”ብሏል።

ከዚህም ባሻገር  የመጂሊስ አመራሮች ወርደዋል ተብሎ ተመሳሳይ አላማ እና አቋም ያላቸውን ሌሎች ሰዎች በቦታው ላይ ለማስቀመጥ የሚሸረብ ሴራ እንዳይኖር መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ያሣሰበው ወረቀቱ፤ ህዝበ-ሙስሊሙ ያነሳቸው ጥያቄዎች በተገቢው እና በትክክለኛው መንገድ እስከሚፈቱ ድረስ  ቅንጣት ታህል እንዳይዘናጋ መክሯል።

ብዙሀኑ የኢትዮጵያ ሙስሊም  ካለፉት ወራት ጀምሮ በተከታታይ እያደረገ ባለው ተቃውሞ ሰልፍ እያቀረባቸው ካሉት ጥያቄዎች መካከል አንዱ፦” አሁን በስልጣን ላይ ያለው መጂሊስ  የመንግስት ተሿሚ እና ጉዳይ አስፈፃሚ እንጂ የሙስሊሞች ወኪል ስላልሆነ  ከቦታው ተነስቶልን ፤እኛ የፈለግነውን መጂሊስ እናቋቁም’ የሚል እንደሆነ ይታወቃል።

ሌላው በዋነኝነት ከብዙሀኑ ሙስሊም የተነሳው ጥያቄ፦”መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ በመግባትና ግፊት በመፍጠር አህባሽ የተሰኘውን አስተምህሮ ለማስፋፋት ከሚያደርገው ጥረት ይቆጠብ” የሚል ነው።

“በአሁኑ ጊዜ የመጂሊስ አባላት ሙሉ በሙሉ እንዲወርዱ ስለመወሰኑ ዜና ቢሰማም፤ገና ተግባራዊነቱ አልተረጋገጠም። የ አህባሽ አስተምህሮን አስመልክቶ ላነሳነው ጥያቄ ገና ምላሽ አላገኘንም።ያነሳናቸው ጥያቄዎች ሳይሸራረፉ በተግባር እንዲመልሱ እንጂ፤ጥገና በሚመስል መልኩ እንዲድበሰበሱ አንፈልግም! ‘አለባብሰው ቢያርሱ፤ በአረም ይመለሱ’ እንዳይሆን፤ህዝበ-ሙስሊሙ  ጥያቄዎቹ በትክክል መመለሳቸውን ሳያረጋግጥ   ከጀመረው መብቱን የማስከበር እንቅስቃሴ አንድ ጋት እንኳ ወደ ሁዋላ ሊል አይገባም” ብለዋል- የተበተነውን ወረቀት ያነበቡ አንድ  ኢማም አዲስ አበባ ለሚገኘው የ ኢሳት ዘጋቢ በሰጡት አስተያዬት።

ኢሳት የተበተነው ወረቀት ከሙስሊሙ ኮሚቴዎች የተላከ ይሁን አይሁን ለማረጋጋጥ አልቻለም፣ ይሁን እንጅ አሁንም በኤስ ኤም ኤስና በፌስቡክ የሚሰራጩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሙስሊሙ ማህበረሰብ የፊታችን አርብ በአንዋር መስጊድ ተመሳሳይ ተቃውሞ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ ነው።

የመለስ መንግስት ከምርጫ 97 በሁዋላ እንዲህ አይነት ከፍተኛ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ አያውቅም። መንግስት በአንድ በኩል ጥያቄውን በሀይል እንደሚፈታ ይዝታል፣ በሌላ በኩል ደግሞ አሸባሪ ከሚላቸው አመራሮች ጋር መደራደር ይፈልጋል።  በመንግስት በኩል የሚታየው በመታገስና ጊዜ በመግዛት የሙስሊሙን ጽናት መፈታተን ፣ አንድነቱንም የመከፋፈል ስትራቴጂ እንዳልሰራ ተንታኞች ይናገራሉ። በአንድ በኩል ሙስሊሙ የሚያሳየው ፍጸሙም ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴና ተገቢ እና ምክንያታዊ የሆነ ጥያቄ፣ በሌላ በኩል ተቃውሞው ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው እና በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ የሚካሄድ በመሆኑ ሙስሊሙን ማህበረሰብ በተራዘመ ትእግስት አዳክማለሁ የሚለው ስልት አለመስራቱን ተንታኞች ያክላሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide