ሚያዚያ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ማኔጅመንትና አሳታሚዎች ውይይት ያለውጤት ተበትኗል፡፡ሁለቱ ወገኖች በድጋሚ ለመወያየት ለግንቦት 10 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮም ይዘዋል፡፡
በትላንትናው ዕለት አሳታሚዎችን የወከሉ አባላት ከብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመገኛኘት “የሕትመት ስታንዳርድ ውል” በሚል እንዲፈርሙ የቀረበላቸው ረቂቅ ውል ሕገመንግሥቱን ጭምር የሚጥስ ቅድመ ምርመራ መሆኑን በመጥቀስ ውሉን ለመፈረም እንደሚቸገሩ የገለጹላቸው ቢሆንም የማተሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ከሕገመንግስቱ ጋር ነገሩ እንደማይገኛኝ ለማስረዳት ከመሞከራቸው ጋር ተያይዞ በጉዳዩ ላይ ይበልጥ ግዜ ወስዶ ለመነጋገር ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ቀጠሮው ተይዟል፡፡
አንድ በስብሰባው ላይ የተገኙ ለዚህ ዘጋቢ እንደተናገሩት ይህ ዕቅድ የብርሃንና ሠላም ሳይሆን ከበላይ የወረደ በመሆኑ በመነጋገር ይፈታል የሚለው ጉዳይ ብዙ ተሰፋ ያለው ጉዳይ አይደለም፡፡“ይህ ሙከራ ባይሳካስ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሕትመት እስከማቆም የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት ያላቸው አሳታሚዎች ቁጥር ብዙ መሆኑን፣ነገር ግን የጋራ አቋም ለግዜው እንዳልተያዘ ተናግረዋል፡፡
ጋዜጦችና መጽሔቶችን የሚያትሙት ማተሚያ ቤቶች ለግል ጋዜጦችና መጽሔቶች አሳታሚዎች የላኩት የሕትመት ውል ቅድመ ምርመራን አንግሶ ሕገ መንግሥቱንና የፕሬስ ነፃነትን የሚፃረር ነው ሲሉ አሣታሚዎች ተቃውመውታል፡፡ አቤቱታቸውንም ለአቶ መለስ ዜናዊ እና ለአታሚዎቹ ሰሞኑን ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide