ሁለት የመካከለኛው ምሥራቅ ዜጎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ መወሰኑ ውሸት ነው ተባለ

ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-በታላቁ የአንዋር መስጊድ  ለፀሎት በተሰበሰቡ ምዕመናን መካከል በመግባት ህገ-ወጥ  ቅስቀሳ ሲያደርጉ እና  በህገ -ወጥ መንገድ ወረቀት ሲበትኑ የተገኙ ሁለት የመካከለኛው ምሥራቅ ዜጎች በ 24  ሰ ዓት ውስጥ ከ አገር እንዲወጡ ተወሰነ በማለት የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ትናንት ያስተላለፈውን ዘገባ የ አዲስ አበባ ነዋሪዎች ፦”የተለመደ ነጭ ውሸት” ሲሉ አጣጣሉት።

በጉዳዩ ዙሪያ የ ኢሳት ዘጋቢዎች ያነጋገሯቸው በርካታ የመዲናይቱ ነዋሪዎች፦” ከመሬት ተነስቶ ንፁሀን ዜጎችን በሽብርተኝነት የሚከስ መንግስት፤  አንዋር መስጊድ ውስጥ ገብተው ህገ-ወጥ ቅስቀሳ  ሲያደርጉና ወረቀት ሲበትኑ የያዛቸውን የውጪ አገር ዜጎች እንዲሁ ዝም ብሎ ከአገር ያስወጣል ማለት የማይመስል  ነጭ ውሸት ነው” እያሉ በኢቲቪ ዜና ፈገግ እየተሰኙ አስተያዬታቸውን  ሰጥተዋል።

ከአገር እንዲወጡ ተደርገዋል የተባሉት ሁለት የውጪ አገር ሰዎች  በደፈናው ፦”የመካከለኛው ምሥራቅ ዜጎች” መባላቸው እና በትክክል የየትኛው አገር ዜጎች እንደሆኑ አለመገለጹም፤ ሌላው የዜናውን ተዓማኒ መሆን እንድንጠይቅ የሚያደርገን  ነጥብ ነው ብለዋል-ነዋሪዎቹ።

በጋዜጠኝነት ሙያ እንደተለመደው ሁሉ የምርመራ ሪፖርት ለማጠናቀር  ወደ  ኢትዮጵያ  ሊገቢ ሲሉ የተያዙትን የስዊድን ጋዜጠኞች፤ “ያለ መግቢያ ወረቀት ከኦጋዴ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች ጋር ወደ አገር ሊገቡ ሞክረዋል” በማለት በሽብርተኝነት የከሰሰ  መንግስት፤ በሙስሊሞች ተቃውሞ  በተወጠረበት  በአሁኑ ጊዜ፦”ተቃውሞው መሀል አመጽ የሚቀሰቅሱ የውጪ ዜጎችን ይዤ እንዲሁ ወደ አገራቸው  አባረርኳቸው” ብሎ በዜና ማሳወጁ፤ባለሥልጣናቱ ምን ያህል የተራ ዱርዬ ተግባር ውስጥ መግባታቸውን ያሳይ ካልሆነ በስተቀር፤ ማንንም የሚያሳምን አይደለም”ሲሉም አክለዋል።

 ሀይማኖታዊ መብታቸውን ለማስከበር ህጋዊ እና ሰላማዊ ጥያቄ እያነሱ ያሉትን ብዙሀን ሙስሊሞች፤ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉ  በውጪ ሀይሎች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መንግስት በተደጋጋሚ ክስ ሲያሰማ መቆየቱን ያስታወሱት  የመዲናይቱ ነዋሪዎች፤ እንደተባለው ሁለቱ የውጪ ዜጎች አመጽ ሲቀሰቅሱ ቢያዙ ኖሮ ለመንግስት ክስ ጥሩ ማስረጃ  በሆኑት ነበር”ብለዋል።

የምን አገር ዜጋ እንደሆኑ ያልተገለጹት እና በኢቲቪ ላይ ህገ-ወጥ ተብለው የቀረቡት የውጪ አገር ዜጎች ፊት ላይ ይታይ የነበረው ድንጋጤ ፦የወንጀለኝነት እና የጥፋተኝነት ሳይሆን፤ “እነዚህ ሰዎች ምን እያረጉን ነው፣እየሆነ ያለው ነገር ምንድነው?”የሚል ግራ መጋባት ይመስላል ብለዋል- የኢቲቪን ዜና የተከታተሉት እነኚሁ አስተያዬት ሰጪዎች።

በመጨረሻም፦“መንግስት አቧራ ለማስነሳት የሚፈልገው ምንም ነፋስ በሌለበት ነው። በ አየር ላይ ምሥማር መምታት አይቻልም። በብዙሀኑ ሙስሊም የተነሳባቸውን ጥያቄ፤በተራ ማጭበርበር ሊያዳፍኑት አይችሉም”ሲሉ አስተያዬታቸውን አጠቃለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide