“የመለስ አምልኮ” የሚል ርእስ ያለው መጽሀፍ ነገ በገበያ ላይ ይውላል

ሚያዚያ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፍትህ ጋዜጣ መሥራችና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በጋዜጣ ላይ ያወጣቸውን ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ፊቸር- ጽሑፎች፣ አርቲክሎች እና ሀገራዊ ኮሜንተሪ- ሂሶች “የመለስ አምልኮ” በሚል ርዕስ የተመረጡ ስብስብ ሥራዎቹን በመድብል መልክ ያዘጋጀ ሲሆን መጽሐፉ በነገው ዕለት በኢትዮጵያ ዋና- ዋና ከተሞች በገበያ ላይ ይውላል፡፡

“የመለስ አምልኮ” መጽሐፍ 255 ገፆችን አካቶ በመጸሐፉ ጀርባ ላይ የቀድሞው የኢፌድሪ ፕሬዝዳንትና በአሁኑ ጊዜ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ  ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እና በመካከለኛው ምሥራቅ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ወኪል የሆነው ነቢዩ ሲራክ-ን አወንታዊ አስተያየት አካቶ ይዞ ለሀገር ውስጥ በ39 ብር ዋጋ በስርጭት ላይ ያገኛል ያሉን ለአሳታሚው ቅርበት ያላቸው ምንጮች በቁጥር ከ15 ሺህ እስከ 20 ሺህ አካባቢ ለመጀመሪያ ሕትመት የበቃ እና በሀገራችን በጋዜጣ ፍጆታ የዋሉ ፊቸር- አርቲክሎች ይታተሙበት ከነበረው ቁጥር የላቀ ነው ብለዋል፡፡

መጽሐፉ በክፍል አንድ “ሀገራዊ ጉዳዮች” በሚለው ውስን ርዕስ ውስጥ ስድስት ፊቸር-አርቲክሎችን የያዘ ሲሆን፡-  “ይድረስ ለአጉራ ዘለል ካድሬ፣ ኢትዮጵያዊው ማነው፣ የሀገር ፍቅር እስከምን ድረስ፣ “ፌዴራሊዝም” ይሄ ከሆነማ፣ ኪራይ ሰብሳቢ ስንል፣ የትግራይ ህዝብ ማነው” ፣ በክፍል ሁለት “የገዢዎች ጦማርና ባህሪያቶቻቸው” በሚለው ንኡስ ርዕስ ውስጥ ደግሞ- “መለስ ዜናዊ ከመይ ቀኒዮም፣ አቦይ ስብሃት ነጋን በጨረፍታ፣ ምነው አባታችን እያወቁ፣ የሀውልቱ ሥር ፖለቲካ፣ ልጆቻችሁ ቻይና ምን እየሰሩ ነው እና የመጽሐፉ ዋቢ ርዕስ የሆነው የመለስ አምልኮ” ይገኝበታል፡፡

በክፍል ሦስት- “ታላላቅ ሀገራዊ ክስተቶች” ንኡስ  ርዕስ ውስጥ ደግሞ- ትዝታ ሚያዚያ 30፣ የፕሮፌሰር አስራት ወይስ የመኢአድ ሙት ዓመት፣ እስክንድር ነጋን ሳስበው ሳስበው ክፍል አንድ፣ ሰኞን ከመለስ ዜናዊ ጋር፣ ኢህአዴግ ምን ያድርግህ፣ ጓደኞቼን መልሱልኝ፣ አኪልዳማው የአይሁድ ወይስ የኢህአዴግ” የሚሉ ፊቸር- አርቲክሎች ተካተውበታል፡፡

በክፍል አራት- “አንዳንድ ነጥቦች ስለፓርቲዎቻችን” ውስን ርዕስ ውስጥ ደግሞ “ኢህአዴግና ሙስና የአንድ ሳንቲም ግልባጮች፣ የብአዴን ሰዓት ስንት ላይ ቆሟል፣ የተቃዋሚዎች ሰፈር እንደምን ከረመ፣ ኦህዴድን በጨረፍታ፣ ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ሲል” የሚሉ አምስት ፊቸር- አርቲክሎችን ይዟል፡፡

በክፍል አምስት “ሕዝባዊ ብሶቶች” በሚለው የመጨረሻው ንኡስ ርዕስ ውስጥ ደግሞ  “ኢትዮጵያኒዝም” ወደ “ቱኒዚያኒዝም” ያልተቋጨው የአብዮቶች ዋዜማ፣ የፀጥታ ጩኸት፣ “ሹክሹክታው” ምንድን ነው፣ እኔም “አሸባሪ ነኝ”፣ ቄሳርም ይደነግጣል፣ ሞት የማይፈሩ ወጣቶች- የሚሉ ከዚህ ቀደም በፍትህ ጋዜጣ ላይ የተስተናገዱ ፊቸር- አርቲክሎች ይገኙበታል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide