ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የ2012ትን የፔን ሽልማት ተቀበለ

ሚያዚያ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፔን አለማቀፍ ሽልማትን  የተቀበለው፧ በባለቤቱ በሰርካለም ፋሲል በኩል ነው።

በአሜሪካ ሙዚየም ኦፍ ናቹራል ሂስተሪ ውስጥ በተደረገው የሽልማት ስነስርአት 500 የሚጠጉ የፔን ኢንተርናሽናል ደጋፊዎችና አባላት ተገኝተዋል።

“እስክንድር ነጋ እጅግ የተደነቀና ደፋር ጋዜጠኛ ነው። እራሱን ለአደጋ እንደሚዳርገው እያወቀ; ብእሩን ከማንሳት ወደ ሁዋላ አላለም።” ሲሉ የፔን አሜሪካን ማእከል ሀላፊ የሆኑት ፒተር ጎድዊን ተናግረዋል።

በሽልማቱ ስነስርአት ላይ የእስክንድር ባለቤት የሆነችው ሌላዋ ጀግና ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል  የእስክንድርን ሽልማት ስትቀበል ባደረገችው ንግግር ፣ እስክንድር በዚህ ቦታ ተገኝቶ ሽልማቱን ቢቀበል ኖሮ ፣ ሽልማቱን በኢትዮጵያ ውስጥ አስከፊ በሆነ እስር ቤት ውስጥ በሚማቅቁት  እና በስደት ላይ በሚገኙት ጋዜጠኞች ስም ይቀበል ነበር  ” ብላለች።

ሰርካለም ይህን ሽልማት የምትቀበለው በኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ነጻነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በወረደበት ወቅት እንደሆነም አክላለች።

የእስክንድር ሽልማት ቢቢሲን ጨምሮ በሌሎች ታዋቂ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀንም ሰፊ የዜና ሽፋን አግኝቷል።

በሌላ ዜና ደግሞ በኢትዮጵያ የሚገኙ የጋዜጣ አሳታሚዎች ብርሀንና ሰላም ያወጣውን አዲስ የቅድመ ምርመራ  ፎርም  እንዲፈርሙ የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ እንደተሰጣቸው ታውቋል።

 አሳታሚዎቹ ሰሞኑን በጋራ ሆነው የብርሀንና ሰላምን ህገደንብ ለመቃወም ቢሞክሩም ፣ ድርጅቱ ግን በተናጠል ለአሳታሚዎች ስልክ እየደወለ “ደንቡን የማትፈርሙ ከሆነ ጋዜጣችሁ አይታተምም “እንዳላቸው ታውቋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide