የአፋር ህዝብ ፓርቲ በክልሉ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አወገዘ

ሚያዚያ ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-ፓርቲው ኤፕሪል 27 ባወጣው መግለጫ ላይ እንደጠቀሰው በክልሉ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ወደ አደገኛ ሁኔታ እየተሸጋገረ ነው ብሎአል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ኤፕሪል 17 በዱብቲ ከተማ በህዝቡ ላይ በፈጸሙት ድብደባ 8 ሴቶችና 12 ወንዶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ፋጡማ ሙሳ የተባለች ሴት ቤቷን የሚያፈርሱባትን ሰራተኞች በመቃወሙዋ በጡቷ ላይ በደረሰባት ከፍተኛ ድብደባ  አሁንም ድረስ በህመም እየተሰቃየች ነው።

በትናንትናው እለት ደግሞ በዱብቲ ከተማ ባሀይሌ መንደር ውስጥ አሊ ኡመር የተባለ ወጣት መገደሉን አስታውሶአል፤ በአፋር ህዝብ እና በመንግስት መካከል ያለው ፍጥጫም መጨመሩን ጠቅሷል። በአዋሽ ተፋሰስ፣ በአፍዴራ ፣ በዶቢ እና በዳሎል አካባቢ ህዝቡ እየተፈናቀለ ለውጭ ኩባንያዎች መሬቱ እየተቸበቸበ ነው በማለትም አክሎአል።

ፓርቲው በመጨረሻም የውጭ ኩባንያዎች የሞራልና የሰብአዊ መብት ልእልናን በማክበር በአስቸኳይ ከአካባቢው እንዲለቁ፣ የመከላከያ ሰራዊት በህዝቡ ላይ የሚፈጽሙትን ግፍ እንዲያቆሙ፣ ሂውማን ራይትስ ወችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመሳሰሉ ድርጅቶች በአካባቢው ተገኝተው እውነታውን እንዲያጣሩ፣ እንዲሁም የአፋር ህዝብ በመንግስት ላይ የሚያደርገውን ተቃውሞ አጠንክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide