ሚያዚያ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ መምህራን እንደተናገሩት መንግስት የደሞዝ ጭማሪ እንዲያደርግ ለማስገደድ የስራ ማቆም አድማ አድርገው እንደነበረ አስታውሰው፣ ይሁን እንጅ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንግስት የበቀል እርምጃ እየወሰደባቸው ነው። እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል መምህርት ሀያት ሙሀመድ፣ መምህር ግርማ ሀይሌ፣ ደገፋው ዘላለም፣ አገር በለው ፣ ደስታ ገብረ እግዚአብሄር፣ አየለ መልካሙ እና ሌሎች ሶስት መምህራን የወር ደሞዛቸውን ተቀጥተዋል።
ሰሞኑን የወረዳው ባለስልጣናት መምህራንን ሰብስበው የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ ያረካል አያረካም በማለት ቢጠይቁም መምህራን ግን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። መምህር ደስታው ገብረ እግዚአብሄር ብቻ ” እኛ ተናግረን ያተረፍነው ነገር ምንድነው? እኛ የጠየቅነው የመብት ጥያቄ ሆኖ እያለ ደሞዛችንን ተቀጣን። ስለዚህ ብንናገር ባንናገር ትርፉ ራስን መጉዳት ነው በማለት።” ተናግረዋል።
ከፍተኛ ውጥረት በታየበት ስብሰባ አንዲት የኢህአዴግ ካድሬ መምህር ” የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ አርኪ በመሆኑ ጭማሪው ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ይዋልልን በማለት በመናገሩዋ።” ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟታል። በደሞዝ ጭማሪው ላይ አስተያየት አንሰጥም ያሉት መምህራን ጥያቄያቸውን ወደ ዋልድባ ገዳም አዙረው እንደነበር ታውቋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን አሁንም ተቃውሞአቸውን ለማሰማት ውስጥ ለውስጥ በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል። መምህራን መንግስት ያደረገው የደሞዝ ጭማሪ ፤ በመምህሩ የስራ ሞራል ላይ ከፍተና ውድቀት እንዳስከተለም መምህራን በመናገር ላይ ናቸው።
___________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide