እስክንድር ነጋና አንዱ አለም አራጌ የቪዲዮ ማስረጃቸውን አቀረቡ

ሚያዚያ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አቃቢ ህግ በእስር ላይ የሚገኙትን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አንዱአለም አራጌን ሆን ብሎ ለመወንጀል የቪዲዮ ማስረጃዎችን ቆራርጦ አቅርቧል በማለት ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ የቆዩት እስረኞች ዛሬ ሙሉ ቪዲዮ በማቅርብ እንዲታይላቸው አድርገዋል።

አቃቢ ህግ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበሩት አቶ አንዱአለም አራጌ የመለስ መንግስት እንዲወገድ የአመጽ ጥሪ መቀስቀሳቸውን ያሳይልኛል ያለውን ቪዲዮ ቀደም ብሎ ማቅረቡ ይታወሳል። አቃቢ ህግ ድምጾችን እና ምስሎችን ለራሱ በሚመች መልኩ በማቅረቡ ተከሳሾቹ ሙሉው ቪዲዮ እንዲቀርብ ሲወተውቱ ነበር። ተከሳሾቹ ሙሉውን ቪዲዮ አዘጋጅተው ማቅረባቸውን ዛሬ ለፍርድ ቤቱ ያስረዱ ቢሆንም አቃቢ ህግ ግን ሙሉው ቪዲዮ መታየት የለበትም በማለት ተከራክሯል። ይሁን እንጅ የማህል ዳኛው አቃቢ ህግ የራሱን ማስረጃዎች ያቀረበ በመሆኑ ተከሳሾችም የራሳቸውን ማስረጃ የማቅረብ መብት ያላቸው በመሆኑ ሊከለከሉ አይገባም በማለት ትእዛዝ ሰጥቶ ቪዲዮዎቹ ቀርበው ታይተዋል።

በቪዲዮዎቹ እንደተመለከተው አንዱአለም አራጌ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የአፈና ስርአት በአረቡ አለም ከታየው ህዝባዊ አመጽ ጋር በማነጻጸር በኢትዮጵያ ውስጥም  በሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን፣ ከሰላማዊ ትግል ውጭ ግን ሌሎች አማራጮች የማይሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። አቶ አንዱአለም ያቀረቡት ሙሉ ቪዲዮ አቃቢ ህግ ያቀረበውን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚያደርግ መሆኑን ችሎቱን የታደሙት ሰዎች ለኢሳት ዘጋቢ ገልጠዋል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም ያቀረበው ቪዲዮ ነጻ ፍርድ ቤት ቢኖር ዛሬውኑ ጋዜጠኛውን ከተከሰሰበት ሽብር የመፈጸም ተግባር ሙሉ በሙሉ ነጻ የሚያወጣው መሆኑን በችሎቱ የታደሙት ሰዎች ገልጠዋል።

የማለዳውን ችሎት የተከታተለው ዘጋቢያችን እንደገለጠው አቃቢ ህግ የፍትህና የነጋድራስ ጋዜጦች አዘጋጆች ችሎቱን የማንቋሸሽ እና አጠቃላይ ሂደቱን ተአማኒነት የሚያሳጣ ዘጋባ እያቀረቡ ነው በማለት ለፍርድ ቤቱ ላቀረበው  ክስ አዘጋጆቹ ለዛሬ ቀርበው መልሳቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ፣ የነጋድራስ አዘጋጅ በችሎቱ ሲገኝ የፍትህ ዋና አዘጋጅ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ ግን ችሎት ሳይገኝ ቀርቷል። ተመስገን ችሎት ያልተገኘው መጥሪያ ስላልቀረበለት መሆኑ በፍርድ ቤቱ ተገልጦ መጥሪያ እንዲላክለትና በሚቀጥለው ቀጠሮ እንዲቀርብ አዟል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ተመስገን ያተመው የራሱን ቃል መሆኑን ለችሎቱ ዛሬም በድጋሜ ቢናግርም ፍርድ ቤቱ ግን እንዳይናገር አዞታል። ዋና አዘጋጀቹ በአቃቢ ህግ ከቀረበባቸው ክስ መካከል የእስክንድር ነጋን ቃል ኣዛብተው አቅርበዋል የሚል ነው።

ችሎቱ ከሰአት በሁዋላም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በጊዜ ጥበት ምክንያት የከሰአቱ የችሎት ውሎ ዘገባ ባለመድረሱ ለማቅረብ አልቻልም።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላለፉት 4 ተከታታይ ቀናት በፍትህ ጋዜጣ አዘጋጆችና አምደኞች ላይ የብእር ዘመቻ ከፍቶባቸዋል። ጋዜጣው ከዚህ ቀደም በአውራምባ ታይምስ ላይ ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ አሁንም ተመስገን የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ እንደሚያገኝ፣ የውጭ ሀይሎች ተላላኪ  መሆኑን እና ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚከሱ ፍሬ ፈርስኪ ሀሳቦች በአዲስ ዘመን ላይ በስፋት ቀርበዋል። ጋዜጠኛ ተመስገን የሚጽፋቸው ጽሁፎች ሁሉ እውነትን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ለኢሳት ገልጧል።

__________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide