ሚያዚያ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ስፈራው ሽጉጤ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከ30 አመት በላይ የኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች አሁንም ሰላማዊ ኑሮአቸውን እየመሩ ነው።
በ2000 ዓ.ም በጉራፌርዳ ወረዳ 22 ሺ 46፣ በሜኒሻሻ 1ሺ 484 ፣ በሜኒት ጎልደያ ደግሞ 1ሺ 520 የአማራ ክልል ተወላጆች መኖራቸውን የገለጡት ፕሬዚዳንቱ ፣ የክልሉ መንግሥት በ2001 ዓ.ም አንድ ሰፋሪ ሁለት ሄክታር የእርሻ መሬትና 1ሺ ካሬ ሜትር የቤት መስሪያ ቦታ እንዲያገኝ መመሪያ ቢወጣም ብዙዎቹ ከ2 እስከ 12 ሄክታር መሬት ነበራቸው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት በ2001 ዓ.ም ባወጣው መመሪያ ከነሐሴ 30 ቀን1999 ድረስ ወደ ዞኑ የገቡ ሰዎች ባሉበት ኑሯቸውን እንዲመሩ ይሁን እንጅ ከነሐሴ 30 ቀን1999 በኋላ ወደ አካባቢው የመጡት ወደ ክልላቸው እንደሚለሱ መመሪያ መውጣቱን ገልጠዋል።
በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ከሚኖሩት 22 ሺ አማሮች መካከል 800 ሰዎች ወደ ክልላቸው እንዲሄዱ መደረጉን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የፌደራሉ መንግስት የአማራ እና የደቡብ ክልል መንግስታትን በማነጋገር ሰዎቹ በሰላም እንዲሸኙ ጥረት ማድረጉን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ይሁን እንጅ 35 ሰዎች በአካባቢው ያለውን ደን በመመንጠራቸው በህግ እንዲጠየቁ ለማድርግ በተጀመረው እንቅስቃሴ ፣ 33 አማሮች ህጋዊ ባለመሆናቸው እንዲወጡ ተድርጓል ብለዋል።
አቶ ሺፈራው በሺዎች የሚቆጠሩ አማሮች ተፈናቅለዋል እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ ሀሰት ነው ብለዋል።
አስተያየት ሸጪዎች እንደሚሉት ግን አንድም ሰው ሆነ አንድ ሺ ሰው በእናት አገሩ እየኖረ ይህ ክልልህ አይደለም ብሎ እንዲወጣ ከተገደደ ያው አገር አልባነትን የሚያሳይ ህገወጥ እርምጃ ነው ይላሉ።
የመገናኛ ብዙህን ከ22 ሺ በላይ አማሮች ከቤንች ማጂ ዞን እንዲወጡ ለማድርግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ሲዘግቡ ቆይተዋል። ድርገቱም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ቁጣን ቀስቅሷል።
_________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide