ባለፉት ሶስት ቀናት ከጉርፋዳ ወረዳ የተባረሩ የአማራ ተወላጆች ደብረብርሀን እና ባህርዳር ደረሱ

መጋቢት ፳፱ (ሃይ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢሳት ዘጋቢዎች እንደገለጡት ከጉርዳፋ ወረዳ ከተባረሩት በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩት የአማራ ተወላጆች መካከል በ8 መኪኖች የተጫኑ ደብረብርሀን ላይ እንዲራገፉ ሲደርግ የተቀሩት ደግሞ ወደ ባህርዳር አምርተዋል። ከሾፌሮቹ ለመረዳት እንደተቻለው ሰዎቹ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷል። ዘጋቢያችን አንዳንዶችን አነጋግሮ እንደዘገበው የሚፈናቀለው የአማራ ተወላጅ ቁጥር የመገናኛ ብዙሀን ከሚዘግቡት በእጅጉ የላቀ ነው።ተፈናቃዮቹ በአንድነት ሆነው ወደ አዲስ አበባ ወይም ወደ ሌሎች ክልሎች ቢሄዱ ችግር ሊፈጥሩ ይችላል ተብሎ በመታሰቡ ፣ ወደ ተለያዩ ቦታዎች መበተን ግድ ብሎአል ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የብአዴን አባል ተናግረዋል። አባሉ እንዳሉት የብአዴን አባላት ድርጊቱን ውስጥ ለውስጥ እየተቃወሙት ቢሆኑም እነ አቶ በረከት ስምኦን ግን ጉዳዩ የህዝብን ትኩረት እንዳይስብ ሰዎቹ ከመሀል ከተማ እንዲርቁ ለማድረግ እየሰሩ ነው በማለት አክለዋል።

ከተለያዩ ቀበሌዎች የተሰባሰቡ የአማራ ተወላጆች “አማራ ኬላ” እየተባለ በሚጠራ ስፍራ እንዲሰባሰቡ ከተደረገ በሁዋላ ወደ ክልላቸው እንደሚጓጓዙ እንደሚደረግ ዘጋቢያችን የላከው መረጃ ያሳያል። አንድ ተፈናቃይ ከአካባቢው ነዋሪ ከሆነች ሴት 2 ልጆችን ወልዶ እንደነበር ተናግሮ፣ አሁን ግን ልጆቹን ለእርሷ ትቶ እንዲፈናቀል መደረጉን  ገልጧል።

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን ለኢሳት የሰጡት ብቸኛው የፓርላማ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ “ድርጊቱ ህገ መንግስቱን ላይ የተቀመጠውን ማንኛውም ዜጋ የመኖሪያ ቦታውን የመምረጥ መብት አለው የሚለውን የሚቃወም፣ አገራችንን እንደገና እንድናውቅ የሚአስገድድ”  ነው ብለዋል።

  በሌላ ዜና ደግሞ ከደቡብ ክልል ጉራፋርዳ ወረዳዎች የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች ከ 80 ሺህ በላይ መድረሱ እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤  ገዥው ፓርቲ ነዋሪዎቹ የተፈናቀሉት የአካባቢውን ተወላጆች  ለመጠበቅ ነው በማለት የኢህአዴግ ልሳኖች እየዘገቡ ነው።

የገዥው ፓርቲ ልሳን የሆነው አይጋ ፎረም የአማራ ተወላጆቹ ወደ መጡበት እንዲመለሱ የተደረበትን ምክንያት ባብራራበት ጽሁፍ የአካባቢው “ኢንዲጂኒየስ” ህዝቦች በአካባቢያቸው በአግባቡ እንዲጠቀሙ እና  የተፈጥሮ መራቆትን ለመከላከል ሲባል ከ 1999 ዓመተ-ምህረት ወዲህ ወደ ስፍራው የመጡ የአማራ ተወላጆች ወደ ክልላቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል ብሏል።

ተፈናቃዮቹ ከመስተዳድሩ ፈቃድ አግኝተውና  አስቸጋሪ የነበረውን አካባቢ አልምተው እየኖሩ መቆየታቸው ይታወቃል።

በመሆኑም አይጋ ፎረም፦” የአካባቢውን ተፈጥሮ ለመከላከል ሲባል ነው” በማለት ለሰዎቹ መፈናቀል  እንደ ሁለተኛ ምክንያት  የጠቀሰው ነጥብ  ስህተት እንደሆነ የፅሁፉ አንባቢዎች ይናገራሉ።

“የትግራይ ተወላጅ ባለሀብቶች  ደቡብን ጨምሮ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተንጣለለ ጋሻ መሬት ይዘው እያረሱ ባሉበት ጊዜ አንድና ሁለት ሄክታር መሬት ላይ ከነልጆቻቸው ኑሯቸውን የመሰረቱ ድሀ አማራዎች ወደመጡበት እንዲመለሱ የተደረገው፤ የአካባቢውን ኢንዲጂኒየስ ህዝቦች ጥቅም ለመጠበቅ ነው መባሉ፤ እጅግ አሳዛኝና ልብን የሚያደማ  የክፉ ዘረኞች አስተሣሰብ እንደሆነ” የኒዮርኩ  አቶ መኩሪያ ግርማ ገልጸዋል።

“ሚዲያው ምነው ዝምታን መረጠ?” በሚል ርዕስ አቶ መኩሪያ ባቀረቡት  ጽሁፋቸው  በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ፤ በቂ የሚዲያ ሽፋን አላገኘም ባይ ናቸው።

የሰሜን አሜሪካ የህወሀት ተጠሪ የሆነውና በቅጽል ስሙ “አባ መላ” ተብሎ የሚጠራው ብርሀኑ ዳምጤ ፦” የተፈናቃዮች ነው እየተባለ የምናየው ፎቶ ውሸት ነው” በማለት በሚዲያ መናገሩን ያወሱት አቶ መኩሪያ፤ የህወሀቱ ተወካይ ከዚህም በላይ፦” ተፈናቃዮቹ ለምን ወደ መኢአድ ጽህፈት ቤት ሄዱ? ለምን ወደ ኦህዴድ፤ ወይም ለምን ወደ መስጊድና ቤተ-ክርስቲያን አልሄዱም?” በማለት ታላቁንና አንገብጋቢውን ጉዳይ ፤የርካሽ ፖለቲካ መጠቀሚያ ሊያደርገው መሞከሩን ጠቅሰዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደፈለጉበት ቦታ የመሄድ መብት ቢኖራቸውም፤ እውነታውና የሆነው  ግን ፤ተፈናቃዮቹን  መኢአድ  ሰብስቦ ያስጠለላቸው ፤መንግስት አልቀበል ብሏቸው ሜዳ ላይ ሲወድቁ  እንደሆነ አቶ መኩሪያ ጠቁመዋል።

አቶ መኩሪያ በጽሁፋቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ከቀድሞ ጀምሮ በአማራው ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ አስፈላጊውን ግፊት እንዲያደርጉ አጽንኦት በመስጠት ጠይቀዋል።

ወይዘሪት ኤሎን ሳምሶን ፦”ቀና በል አማራ”በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሁፍ ደግሞ፦  የአቶ መለስ መንግስት ባለፉት 20 ዓመታት አማራውን ለመቅበር ሲባዝን መክረሙንና ጀነራል ሳሞራ ዩኑስ ሳይቀሩ በአንድ ወቅት “አማራውን ቀብረነዋል” ማለታቸውን በማስታወስ፤ “ወያነ ጉድጓድ ሲምስ ከረመ እንጂ፤አማራውን አልቀበረውም”ብለዋል።

ወይዘሪት ኤሎን አያይዘውም፦”እንኳን በቁጥር አናሳ የሆኑት ህወሀቶች ብዙዎቹን አማራዎች ሊቀብሩ ቀርቶ፤ በጊዜው መላውን ጀርመን ከጎኑ ያሰለፈው አዶልፍ ሂትለር፤አናሳዎቹን አይሁዶች ሊቀብራቸው አልቻለም”ብለዋል።

 

 “በአማራ ሊይ አፉን ካልከፈተ ፖለቲካ ያወቀ የማይመስለው ፖለቲከኛ ሁለ ላለፉት 20 አመታት የአማራውን ስነ-ልቦና ለመስበር ተረታ ተረቱን ሲደርት አማራው ከንቀት በስተቀር መልስ አልሰጠውም”ያሉት ወይዘሪት ኤሎን፤አንዳንዶች ይህን ትእግስት ፍርሀት ነው ቢሉትም፤ ታሪክን አብጠርጥረው የሚያወቁ ግን የታላቅነት ስነ ልቦና የፈጠረው መሆኑን ይናገራሉ”ብለዋል።

 

ይሁንና ፤ ትዕግስቱና አስተዋይነቱ ከመስፋቱ የተነሳ በጠባብ ዘረኞች እየተፈፀመበት ያለው ግፍና መከራ ከጽዋው አንገት ተርፎ መሬት መፍሰስ መጀመሩን በዝርዝር ያመለከቱት ወይዘሪት ኤሎን፤ አማራው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በመቆም የጭቆናውን አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመገርሰስ በእልክ፣ በህብረትና በጽናት ሊነሳ እምደሚገባ መክረዋል።

________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide