ሚድሮክ ወርቅ በጉጂና በቦረና ዞኖች ነዋሪዎችን ለማፈናቀል ማቀዱ ተቃውሞ አስነሳ

መጋቢት ፳፭ (ሃይ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሻኪሶ ወረዳ በሬጂ ቀበሌ፣ በሰባ ቦሩ ወረዳ በ ቡሪ ኢጄርሳ ቀበሌ እንዲሁም በቦረና ዞን  በመልካ ሶዳ ወረዳ ሀሎ መጣዳ ቀበሌ ስር የሚገኙ ኤቢቻ፣ ሎቶሪ፣ ኦኮቴ፣ ኦዳ ሀንቃሪ ፣  ደዳቡቱ እና አዩ ቦዳ ቀበሌዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች   የካሳ ክፍያ እና  የመስፈሪያ ቦታ  ሳይሰጣቸው አካባቢውን ለሚድሮክ ኢትዮጵያ አስረክበው እንዲወጡ በመታዘዛቸው የአካባቢው ነዋሪዎች “አካባቢውን ለቀን አንወጣም በማለት” ተቃውሞአቸውን እየገለጡ ነው። 

የሼክ ሙሀመድ ሁሴን አላሙዲን ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ላለፉት 15 አመታት በለገደንቢ የወርቅ ማእድኑ አማካኝነት በእየአመቱ ከ450 ኩንታል በላይ ወርቅ ወደ ውጭ በመላክ ሲሸጥ ቆይቷል። ኩባንያው በእየአመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ትርፍ ቢያገኝም ለአካባቢው ነዋሪዎች የተረፋቸው ጥፋት ብቻ መሆኑን  የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ኩባንያው ከህዝቡ የደረሰበትን ተቃውሞ ወደ ጎን በማለት በፌደራል ፖሊስ እየታጀበ የሚያካሂደውን የወርቅ ፍለጋ በመቀጠል አሁን ደግሞ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን  ያለምንም የካሳ ክፍያ እና የመስፈሪያ ቦታ ለማፈናቀል የሚያደርገው እንቅስቃሴ አሳዛኝ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጠዋል።

ከሁለት አመት በፊት የሻኪሶ አካባቢ ነዋሪዎች ሚድሮክ የአካባቢውን ወርቅ ከማውጣት በስተቀር ለህዝቡ የሰራለት ነገር የለም በሚል ተቃውሞ አንስተው ከ100 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በህገመንግስት ግልበጣና በሽብረተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት በመመላለስ ላይ ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በዚሁ አካባቢ የአንድነት ልሳን የሆነውን የፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ ሲያከፋፍል የተገኘ አንድ ግለሰብ የአካባቢውን ህዝብ ለአመጽ ለማነሳሳት እየቀሰቀስክ ነው በሚል ምክንያት መታሰሩ ታውቋል። በሽር ባሳየ የተባለው የአካባቢው ነዋሪ ከለፉት 20 ቀናት ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን ህዝቡን ለአመጽ እና ለሽብር በማነሳሳት ክስ እንደተመሰረተበት ታውቋል።

መንግስት በመላ አገሪቱ ህዝብ እያፈናቀለ  ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለውጭ አገር ባለሀብቶች እየሰጠ ነው የሚል ተቃውሞ በተደጋጋሚ ይቀርብበታል።

_______________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide