ለሚድሮክ ኩባንያ ሲባል በኦሮሚያ ክልል በቦረና እና ጉጂ ዞን ቀበሌዎች ተፈናቀሉ

መጋቢት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ለሚድሮክ ኩባንያ ሲባል በኦሮሚያ ክልል በቦረና እና ጉጂ ዞን ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች፤ ያለ ምንም ካሳ ከቦታቸው እንዲፈናቀሉ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገለፁ፡፡

ነዋሪዎቹ ለፍኖተ ነፃነት እንደተናገሩት፤ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ፤አካባቢው በወርቅ ማዕድን የበለፀገ በመሆኑ የሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ንብረት ለሆነው ለሚድሮክ ወርቅና ማዕድን ኩባንያ  ለመስጠት  መንግስት በመወሰኑ ነው፡፡

ቀደም ሲል በተመሣሳይ ምክንያት በጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ  የሬጂ ቀበሌ ነዋሪዎች ከቀያቸውና ከሚተዳደሩበት ማሳ ያለምንም ካሳ እንዲነሱ በመደረጋቸው ከነቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ተጠቁሟል፡

እንዲሁም በዚሁ  በጉጂ ዞን በሳቦሩ ወረዳ የቡሪ ካሮና የቡሪ ኤጀርሳ ቀበሌ ነዋሪዎችም በተመሣሳይ መንገድ ከይዞታቸው መፈናቀላቸው ተመልክቷል።

በቦረና ዞን በመልካ ሶዳ ወረዳ  የሀሎ መዴዳ ቀበሌና የኤዲቻ፣ ሎቶሪ፣ አኮቴ፣ ኦዳ፣ ሀንቃሬና ዳዳቡዱ አካባቢ ነዋሪዎች ደግሞ በቶሎ ከ ይዞታቸው  እንዲነሱ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በተመሣሳይ መልኩ ከአሬሮ ወረዳ በቢቢሌ ቀበሌና ዋዩ ቦዳ በሚባል አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችም ያለምንም ካሳና ቅድመ ዝግጅት በአስቸኳይ ከቦታቸው እንዲነሱ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

ቀደም ካለ ጊዜ ጀምሮም ቢሆን  መንግሥት ለሚድሮክ ኩባንያ የነዋሪዎችን ማሳ ሲሰጥ ፤ አካባቢውን እንደሚያለማና ነዋሪዎቹን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ቃል በመግባት ቢሆንም፤  በተግባር ግን ያለውን  ነገር ሲፈጽም አልታየም ሲሉ ነዋሪዎቹ ቅሬታቸውን ይገልፃሉ።

በህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጠው  ንብረት የማፍራትና ከቦታችን ያለመፈናቀል  ዜግነታዊ መብታችን እየተጣሰ ነው  ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች አቤቱታቸውን አሠምተዋል።

 ነዋሪዎቹ ያለፍላጎታቸው እንዲፈናቀሉ  በማድረጉ ሂደት የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር በማስገደድና በማስፈራራት ትልቁን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ከፍኖት ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide