በጥንታዊ ና ታሪካዊ ገዳማት ላይ እየተከሰተ ያለው ተከታታይ አደጋ ቁጣ እየቀሰቀሰ ነው

መጋቢት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በቅርብ ጊዜ ብቻ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ይዞታ ስር ባሉ በሦስት ታሪካዊና ጥንታዊ ገዳማት ላይ ከአስር ጊዜ በላይ  የቃጠሎ አደጋ ተከስቷል።

በጣና ሀይቅ ዳርቻ በምትገኘው በ ኡራ ኪዳነ-ምህረት፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሚገኘው አሰቦት እና በደብረዘይት አቅራቢያ በሚገኘው በዝቋላ ገዳማት። በተለይ ሰሞኑን በዝቋላ የተነሳው ቃጠሎ በህብረተሰቡ ከፍተኛ ርብርብ ቢደረግበትም  እነሆ ሳይጠፋ ሰባተኛ ቀኑን አስቆጥሯል። የእምነቱ ተከታዮች፤መንግስት እሳቱን በማጥፋት ሂደት ተገቢውን እገዛ አላደረገም ባይ ናቸው።

ከወራት በፊት በጣና ደሴት ላይ በምትገኘው በኡራ ኪዳነ-ምህረት ተመሣሳይ ቃጠሎ መከሰቱ ብዙዎችን ማስደንገጡ ይታወሳል።

በኡራ ኪዳነ ምህረት ለተነሳው ቃጠሎ መንስኤው ምን እንደሆነ በይፋ ባይገለጽም፤ የመነኮሳት ልብስ ለብሰው ወደ ገዳሙ የገቡ ሰዎች እሳቱን ሳይለኩሱት እንዳልቀሩ የገዳሙ መነኮሳት ሲናገሩ ተደምጠዋል።እነዚያ  ሰዎች እነ ማን?ወይም የነ ማን ናቸው? የሚለው ግን እስካሁን ዕንቆቅልሽ እንደሆነ ቆይቷል።

ይህ ዕንቆቅልሽ  ባልተፈታበት ሁኔታ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሚገኘው የአሰቦት ገዳም  ለአምስት ጊዜ በተደጋጋሚ  እሳት ተነስቶ  የገዳሙ ይዞታ የሆነንና በሰፊ መሬት ላይ የነበረ ደንን አወደመ።

የገዳሙ መነኩሴ  ባህታዊ አየለ ገብረፃድቅ ለ ቪኦኤ የ አማርኛው ክፍል እንደተናገሩት እስካሁን የ እሳቱ መንስኤ ምን እንደሆነ አልታወቀም።

ይህ በ እንዲህ እንዳለ በምዕራብ ሐረርጌ ሜኤሶ ወረዳ በአሰቦት ሥላሴና አባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም የአብነት ተማሪ የሆነው የ7 ዓመቱ ሕፃን ናታን አንበስ  ትናንት ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በ3 ጥይት ተመትቶ መገደሉን የገዳሙ ዋና መጋቢና ምክትል አበምኔት አባ ዘወልደ ማርያም ገልጸዋል።

 አበምኔቱ እንዳሉት  ታዳጊ ህፃኑ ከአባ ሳሙኤል ገዳም በተወሰኑ ሜትሮች ርቀት ላይ ከእናቱ ጋር ወደ ገዳሙ በመውጣት ላይ እያለ  ነው ታጣቂዎቹ ከእናቱ እጅ ቀምተው በመውሰድ ፊት ለፊቷ በሦስት ጥይት ገድለውት የተሰወሩት።  በእናትየው ጩኸትና በጥይት ድምጽ የተደናገጡት መነኮሳት ገዳዮቹን ለመያዝ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል-እንደ ማህበረ-ቅዱሳን ድረ-ገጽ ዘገባ።

  ሰሞኑን በዝቋላ ገዳም  የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት ወደ ሥፍራው ከተመሙት የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል አንድኛው በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት እንደቆሰለ መዘገቡ አይዘነጋም።

ፖሊስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪውን በጥይት የመታው፤  በስፍራው በተሰበሰቡ ወጣቶች እና በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ መካከል በተቀሰቀሰ አለመግባባት ጣልቃ በመግባት ነው።

 ደጄ ሰላም እንዳለው ፤የአለመግባባቱ መንሥኤ ፤ጋዜጠኛው ቃጠሎውን አስመልክቶ በቀጥታ ስርጭት  እሳቱ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ አስመስሎ ያስተላለፈውን ዘገባ ወጣቶቹ በመቃወማቸው ነው።

ከተቀሰቀሰ አራተኛ ቀኑን ያስቆጠረው እሳት ከሁለት ቀን በፊት  እንደ አዲስ አገርሽቶ “ ህዝቡ” በሚችለው አቅም ወደ ዝቋላ  እንዲወጣ ጥሪ በቀረበበት  ዕለት ነበር ጋዜኛው እሳቱ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ሲዘግብ የነበረው።

በመንግስት ሚዲያ ዘገባዎች  ተዓማኒነት ላይ ተስፋቸው የተሟጠጠ እጅግ ብዙ ኢት ጵያውያን፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሀቅ ይዘቱ ሳይዛባ በትክክል የሚተላለፍ ፕሮግራም ቢኖር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ነው ሲሉ ይደመጣሉ።

እንደ ድረ- ገፁ ዘገባ፤በዩኒቨርሲቲ ተማሪው ላይ ከደረሰው የመቍሰል አደጋ ውጭ ከትላንትናው ዕለት ጀምሮ ቃጠሎውን ለመከላከል በየሸጣሸጡና በየገደሉ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች የመውደቅ፣ የመሰበር እና የመላላጥ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የመቁሰል አደጋ የደረሰበት ተማሪ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ህክምና እየተከታተለ እንደሚገኝ ታውቋል። ዘግይቶ በደረሰን ዜና መሰረት በዝቋላ እሳት ለማጥፋት ሄደው በፖሊስ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ወጣቶች ሦስት ደርሰዋል።  

ይህ በእንዲህ እንዳለ   ወደ ዝቋላ ገዳም ከተለያዩ ከተሞች የሚሄዱ መኪኖች “ድሬ” በተባለችው መዳረሻ ከተማ ላይ በፖሊስ መታገዳቸው ተሰምቷል፡፡

ተጓዦቹ ለመታገዳቸው የተሰጣቸውው ምክንያትም፦ ‹‹የሚሄደው ሰው በጣም ስለበዛ አንዳንዶች በዚህ ተጠቅመው የሚያደርሱትን ጉዳት ለመከላከል ነው፤›› የሚል እንደሆነ ተናግረዋል።

ሰዎቹ  ወደ ሥፍራው እንዳይሄዱ የታገዱት፤የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት  ግብረ ሀይል የሆኑ በስፍራው የሚገኙ ባለሞያዎች፤ እሳቱ  ካለበት ደረጃ እንዳይዛመት ግንድ እየተቆረጠ መሠራት ለሚገባው  እሳቱን  የመግታት(fire break)ሥራ ከፍተኛ የሰው ጉልበት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን እየገለጹ ባለበት ጊዜ ነው:፡

ከዚህም ሌላ ሰሞኑን ከዋልድባ ገዳም የተመለሱት የቤተ-ክህነቱ ሀላፊ ቃጠሎውን ለማጥፋት የሚያግዝ ሄሊኮፕተር እንዲፈቀድ ወደ አየር ሀይል አቅንተው ጥያቄ ማቅረባቸው ቢሰማም፤ እሳቱን በማጥፋቱ ሂደት ላይ ከአየር ሀይል የተሳተፈ አንድም ሄሊኮፕተር የለም።

እንዲሀም እሳቱን ለማጥፋት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል የተባለና በመንግስት እጅ ብቻ የሚገኝ ኬሚካል እንዲቀርብላቸው  አስተባባሪዎቹ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱ ተመልክቷል።

በ እሳት መከላከሉ ሥራ ላይ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ከፍተኛውን ተነሳሽነትና ሀላፊነት በመውሰድ ከእቶን እሳት ጋር ግብ ግብ የገጠሙት፤ የገዳሙ መነኮሳት፣ የቤተክርስቲያኗ ወጣት ልጆችና ምዕመኖቿ መሆናቸው ታውቋል።

  ይህም ሆኖ ፤የቃጠሎውን መዛመት ለመግታት እየተቆረጠ የሚሠራው ማገጃ (አረፍተ እሳተ) ለጊዜውም ቢሆን ከቃጠሎ ተርፎ ለሚታየው የደኑ ክፍል መራቆት ምክንያት እየሆነ ነው-ይላሉ የሥራው አስተባባሪ ወጣቶች።

 ‹‹ይህ ሁሉ በአየር መከላከል ቢታገዝ የግማሽ ሰዓት ሥራ ይሆን ነበር፤›› ያለው አንድ ወጣት፤ መነኰሳቱ አረፍተ እሳቱን ለመሥራት ዛፉን የሚቆርጡት፦ ገዳማችንን አራቆትነው” እያሉ  እያነቡ ጭምር  – እንደነበር መመልከቱን ተናግሯል።

መንግስት እሳቱን ለማጥፋት ሀላፊነቱን አልተወጣም፤ዳተኝነት አሳይቷል የሚል አቋም የያዙ ምሽመናን በውጪ አገሮች ከሚኖሩ የ እምነቱ ተከታዮች ጋር በመሆን ዝቋላን ገዳምን ለመታደግና በነበረ ይዞታው ለማስቀጠል ዓለማቀፍ ኮሚቴ ማቋቋማቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል መንግስት በዋልድባ ገዳም ውስጥ ምንም ዓይነት የስኳር ልማት ፕሮጀክት አላካሄደም፤ለማካሄድም እቅድ የለውም ሲሉ አቶ አባይ ፀሀዬ ተናገሩ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ይህን የተናገሩት ሰሞኑን የዋልድባ ገዳምንና  በ አካባቢው ሊሠራ የታቀደውን የሥኳር ልማት ፕሮጀክት ሄደው ከጎበኙ በሁዋላ   በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተገኝተው በሰጡት መግለጫ ነው።

በገዳሙ መነኮሳትና በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የቀረበውን ተቃውሞም፦” አግባብ ባለው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር መሠረት ያልቀረበ፣ ሌላ አጀንዳ ባላቸው ሀይሎች የተቀሰቀሰ፣ ትርጉም የሌለውና ተገቢ ያልሆነ “ በማለት ሲያጣጥሉት ተደምጠዋል-አቶ አባይ ፀሀዬ።

አቶ አባይ ይህን ቢሉም ከሚመሩት ኮርፖሬሽን የወጣው መረጃ   የወልቃይት የስኳር ልማት ፕሮጀክት የሚካሄደው የዋልድባን ገዳም ከከበቡት ወንዞች አንዱ በሆነው የዛሬማ ወንዝ ላይ እንደሆነ ነው የሚያመለክተው።

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  የዜና እወጃ ምሽት ላይ ስቱዲዮ ተገኝተው በገዳሙ ላይ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ በገዳሙና በስኳር ፕሮጀክቱ መካከል የስድስት ሰዓት ያህል ርቀት የሚገኝ  እንደሆነና  ቅዱስነቱ ሳይነካ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ይሁንና  ፕሮጀክቱ በፍፁም  ገዳሙን አልነካም፤አይነካምም ያሉት አቶ አባይ ብዙም ሳይቆዩ  በስፍራው ያረፈ የሰዎች አጽም በክብር እየተነሳ እንደሆነ እና በፕሮጀክቱ ምክንያት ከስፍራው የሚነሱ ሰዎች ወደ ሌላ ቦታ በሚዛወሩበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደተደረገ ተናግረዋል።

የዋልድባ መነኮሳት፤ ተጠብቆ የቆየው ቅዱስ  ገዳማቸው በስኳር ፕሮጀክት ግንባታ ሳቢያ እየታረሰ፣ የቅዱሳን አባቶች አጽም እየፈለሰ፣ መቃብራቸው እየተደፈረና የጥርጊያ መንገድ እየወጣበት መሆኑን በመጥቀስ  መፍትሔ እንዲሰጣቸው  መጠየቃቸው  ይታወሳል።

በ አቶ አባይ ጸሀዬ መግለጫ ውስጥ ሌላው አስገራሚው ነገር፤ የስኳር ፕሮጀክቶች ከሚገነባባቸው ቦታዎች አንዱ የሆነው የወልቃይት ወረዳ ‘በትግራይ ክልል እንደሚገኝ መጠቀሱ ነው።

የመንግስት ሚዲያዎች እና ሪፖርተር ጋዜጣ የ አቶ አባይ ፀሀዬን መግለጫ በመቀበል  ‘በትግራይ ክልል በሚገኘው የወልቃይት ወረዳ የስኳር ልማት ይገነባል”ብለው እየዘገቡ ነው።  

ሰፊና ጾም ያደረ እጅግ ሰፊ መሬት ባላት አገር ላይ ታሪካዊ ቦታዎች ለልማት እየተባሉ መታረሳቸው ህዝባዊ ቁጣ ቀስቅሷል።

በተለይ የገዳሙ መነኮሳት “እንሞታለን እንጂ፤ በህይወት እያለን ቅዱስ መካናችንን” አናስነካም” በሚለው አቋማቸው እንደፀኑ መሆናቸውን በስፍራው የሚገኘው የ ኢሳት ወኪል ዘገባ ያመለክታል።

 በገዳሙ ዙሪያ የሚኖረው የሰሜን ጎንደር ህዝብም መንግሰት ቀዱስ ገዳማችንን እያረከሰው ያለው ሀይማኖታችንንም፤እኛንም ስለናቀን ነው። ከዚህ በላይ ምን ሞት አለ? እያለ በቁጣ በማጉረምረም ላይ መሆኑንም አመልክቷል።

ሁኔታው  ወደ አደገኛ አቅጣጫ እያመራ መሆኑን እየተከታተሉ ያሉ ገለልተኛ ወገኖች፤ መንግስት የሚያከናውነውናቸው የልማት ተግባራት ከህዝቡ እምነት፤ ባህልና እሴቶች ጋር እንዳይጋጩ ፤ቢጋጩ እንኳ ቅራኔያቸው የከፋ ውጤት የማያስከትልበትን መንገድ በመተለም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት በተደጋጋሚ ሢያስጠነቅቁ ይሰማሉ።

ይሁንና መንግስት የዚህ ዓይነት ቅራኔዎችን በብልሀትና በትዕግስት ለመፍታት ዝግጁነት ያለው አይመስልም።

አቶ አባይ ጸሀዬ  በገዳሙ ዙሪያ የመነኮሳቱንና የእምነቱን ተከታዮች  ቅሬታ፦” ሌላ ስውር አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ያነሱት ፤ትርጉም የለሽ ተቃውሞ” በማለት ሢያጣጥሉት የተደመጡት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቻ አዲሱን ሊዝ አዋጅ አስመልክቶ ህዝቡ እያሰማ ላለው ቅሬታ፤ መጂሊስና አህባሽ አይወክሉንም በማለት ሙስሊሙ ህብረተሰብ ላነሳው ተቃውሞ፣በጋምቤላ የሚካሄደውን የግዳጅ ሰፈራና ማፈናቀል አስመልክቶ በህዝቡ ዘንድ እየተነሳ ላለው ጥያቄ መንግስት የሰጠው ምላሽ አቶ አባይ በዋልድባ ለተነሳው ተቃውሞ ከሰጡት መልስ ጋር ተመሣሳይ ነው- “ይህን ተቃውሞና ጥያቄ የሚያነሱት የራሳቸው ፖቲካዊ አጀንዳ ያላቸው ጥቂት ቡድኖች ናቸው” የሚል።

እናም መንግስት ተቃውሞዎችን በውይይት በመፍታት ሳይሆን በቁጣ በመደፍጠጥ በራሱ መንገድ ማረሱን ቀጥሏል። ከመታረስ በተረፉት የቤተ ክርስቲያን ይዞታ በሆኑ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት ላይ ደግሞ እነሆ  የቃጠሎ አደጋ ተደቅኗል። ግራኝ አህመድ ከሞተ ከመቶ ዓመታት በሁዋላ ኡራ ኪዳነ ምህረት፣አሰቦትና ዝቋላ  የእሳት ሰለባ ሆነዋል።

ነገስ ተረኛው ገዳም ወይም ታሪካዊ ስፍራ ማን ይሆን? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑን ቀጥሏል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide