ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ጥቃት መሰንዘሩዋን አስታወቀች

መጋቢት 6 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት ባወጣው መግለጫ የኤርትራ መንግሥትና ተላላኪዎቹን የጥፋት ተልዕኮ ማዕከላትን ዛሬ ማለዳ ላይ አውድሟል ብሎአል።

የሚኒስቴሩ የኢንዶክትሬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ማዕከል ኃላፊ ኮሎኔል ገብረ ኪዳን ገብረ ማርያም  ከኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ባሉት ራሚድ፣ገላሃቤና ጌምቤ በተባሉ ሥፍራዎች ተሰባስቦ የነበረውን ኃይል ሙሉ በሙሉ አውድሟል ብሎአል።

ሠራዊቱ የኤርትራ መንግሥትና ተላላኪዎቹን የጥፋት ተልዕኮ ለማክሸፍ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ለማድረስ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ካልተቆጠበ በስተቀር ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰዱን ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ዓይነት ድርጊት እንዳይደገም ሁኔታውን ስታጠና መቆየቷንና ለዚህም ተመጣጣኝ ነው የምትለውን እርምጃ መውሰዷን ኃላፊው አመልክተዋል።

አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው እርምጃው የተወሰደው በቅርቡ በአፋር አካባቢ 2 ቱሪስቶች መጠለፋቸውንና 5 መሞታቸውን ተከትሎ ነው ብለዋል

የኢትዮጵያ መንግስት የተሳካ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸሙን ይናገር እንጅ በጥቃቱ ምን ያክል ወታደሮችን እንደገደለ የተናገረው ነገር የለም። የኢትዮጵያ ሰራዊት 18 ኪሎሜትር ወደ ኤርትራ ድንበር ገብቶ ጥቃት መፈጸሙ ተነግሯል።

ኢሳት ከወራት በፊት በርካታ የመካላከያ ሰራዊት የጫኑ መኪኖች ወደ ድንበር ማቅናታቸውን መዘገቡ ይታወሳል። 

የኤርትራ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው መልስ የለም። የኤርትራን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው መኩራም አልተሳካም።

ኢትዮጵያ ጡሩዋን ሶማሊያ በመላክ ከአልሸባብ ጋር በመዋጋት ላይ መሆኑዋ ይታወቃል። የተወሰነው ሰራዊት ደግሞ በሰላም አስከባሪ ስም ደቡብ ሱዳንና ዳርፉር ውስጥ ይገኛል።ኤርትራ ለኢትዮጵያ ጥቃት የአጸፋ መልስ የምትሰጥ ከሆነ ኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ ከኤርትራ እና በምስራቅ ደግሞ ከአልሸባብ ጋር መፋለም ግድ ይላታል።

በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል የሚታየው ፍጥጫ ወደ ሙሉ ጦርነት ካመራ በሁለቱ አገሮች ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ምስቅልቅል እንደሚፈጠር ተንታኞች ይናገራሉ።  አሁን በሚታየው የኑሮ ውድነት ማንኛውም ጦርነት የኢትዮጵያውያንን ህይወት ገሀነም ውስጥ ይከተዋል ሲሉ ተንታኞች ያስጠነቅቃሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide