በጋምቤላ የተፈጸመው በመንግስት ሀይሎች ሳይሆን አይቀርም ተባለ

መጋቢት 6 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-በጋምቤላ ባለፈው ሰኞ በተፈጸመው ጥቃት ከ30 በላይ በብዛት የጋምቤላ ኮሌጅ ተማሪዎች የሆኑትን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውቶቡስ ተጠልፎ፣ 19 ሰዎች ከተገደሉና 8 ሰዎች ደግሞ ከቆሰሉ በሁዋላ ድርጊቱን የፈጸሙትን ሰዎች ለማጣራት የኢሳት የጋምቤላ ዘጋቢ ላይ ታች ሲል ቆይቷል።

ዘጋቢያችን ባደረሰን መረጃ ለጥቃቱ ምናልባትም የክልሉ ባለስልጣናት ወይም የፌደራል መንግስቱ እጅ ሳይኖርበት አይቀርም።

ትናንት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወደ ጋምቤላ ኮሌጅ በመጓዝ ተማሪዎች ድርጊቱን በሰላማዊ ሰልፍ እንዲያወግዙና የክልሉ ባለስልጣናትም ሆነ የፌደራል መንግስቱ እጅ የለበትም ብለው እንዲናገሩ ለማግባባት ወደ ኮሌጁ አምርተው ከተማሪዎች ጋር ተነጋግረዋል። ተማሪዎች በበኩላቸው ድርጊቱን የፈጸሙት እነማን እንደሆኑ በትክክል ለማወቅ ባልተቻለበት ሁኔታ የተቃውሞ ሰልፍ የምናደርግበት ነገር አይኖርም በማለት መልስ ሰጥተዋል። በዚህም የተነሳ ለዛሬ ወይም ለነገ ሊደረግ የነበረው ሰልፍ ሊካሄድ እንደማይችል ታውቋል። 

የመንግስት ባለስልጣናቱ በድርጊቱ የመንግስት እጅ የለበትም ብለው እንዲናገሩ ለማግባባት ለምን ፈለጉ? በማለት የሚጠይቀው ዘጋቢያችን ምናልባትም በክልሉ ውስጥ ድርጊቱን የሚያቀናብሩት የክልሉ እና የፌደራል መንግስቱ ናቸው በማለት የሚወራውን ወሬ ለማብረድ ወይም አንድ ነገር ለመሸፋፈን የሚደርግ ሙከራ ይመስላል ብሎአል። የጋምቤላ ኮሌጅ ተማሪዎች እንዲህ አይነት አሰቃቂ ድርጊት ተፈጽሞ ለማውገዝ አለመነሳሳታቸው በጥቃቱ ዙሪያ ያለውን ብዥታ የሚያሳይ ነው።

የሟቾችን እስከሬን በጫነው መኪና ላይ “መልስ ካልተሰጠን ለሚመለከተው ሁሉ እናመለክታለን” የሚለው ባነርም አንድ ጥርጣሬ የሚያጭር ነው ሲል አክሎአል።

ከሁሉም በላይ ጥቃቱን የፈጸሙት የፌደራል ፖሊስ አባላትን ዩኒፎርም የለበሱ መሆናቸው፣ እንዲሁም በጥቃቱ ቦታ ፈጥነው የተላኩት ተመሳሳይ ልብስ የለበሱ የፌደራል ፖሊስ አባላት መሆናቸው እና እርስ በርስ ለመለያየት አለመቻላቸው እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ አባላት ከእኛ የተለየ ዩኒፎርም የለበሱ መከላከያዎች ቢላኩ ኖሮ ታጣቂዎችን በቀላሉ ለመምታት ይቻል ነበር በማለት ያነሱት ጥያቄ ጥቃቱ ሆን ተብሎ የተቀናበረ ሊሆን እንደሚችል ዘጋቢያችን ጠቅሷል።

እነዚህ ታጣቂዎች የፌደራል የደንብ ልብሶችን ከየት አገኙ? የተወሰኑ ሰዎች ልብሱን በተለያየ መንገድ ለማግኘት ይቻላቸው ይሆናል፣ በሁለትና ሶስት መቶ ኪሎሜትሮች በሚፈጸመው ጥቃት ሁሉ የፌደራል ልብስ የለበሱ ሰዎች የሚፈጽሙት ከሆነ ፣ ልብሱን ያዘጋጁት የልብሱ ባለቤቶች ሊሆኑ ይችላሉ ይላል።

መንግስት ጥቃቱን ፈጽሞ ከሆነ ለምን አላማ እንደፈጸመ ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑንም ዘጋቢያችን ሳይጠቅስ አላለፈም። ማናልባትም በደቡብ ሱዳን ላይ ጠንካራ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ ወይም የክልሉን ባለስልጣናት ጸጥታውን አልተቆጣጠራችሁም ብሎ ለማውረድ ወይም አካባቢውን ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግስቱ ስር በማድረግ የመሬት መስጠቱን ስራ ለማፋጠን ይሆናል ሲል መላምቶችን አስቀምጧል።

በሌላ በኩል ደግሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኦሞድ ኦቦንግ ጥቃቱ የተፈጸመው ደቡብ ሱዳን ውስጥ የቆዩ በ1996 በክልሉ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ ፈጽመው የተሰደዱ ናቸው ብለዋል።

በቅርቡ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ወደ ደቡብ ሱዳን በማቅናት ለደቡብ ሱዳን መንግስት ከባድ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide