መጋቢት 1 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በጠና ታመው ኮሪያ ሆስፒታል መግባታቸውን አዲስ አድማስ ዘገበ።
ላለፉት 11 ዓመታት በኢትዮጵያ ርዕሰ ብሄርነት የቆዩት መቶ አለቃ ግርማ፤ የሥራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ከሥልጣን ለመውረድ የስድስት ወራት ዕድሜ ቀርቷቸዋል።
ይሁንና ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን በመሰናበቻቸው ዋዜማ በጠና ታመው በኮሪያ ሆስፒታል የቅርብ እርዳታና ክትትል እየተደረገላቸው ነው።
የሆስፒታሉ ምንጮች ለጋዜጣው እንደጠቆሙት፤ ፕሬዚዳንቱ ከትናንት በስቲያ በጠና ታመው ወደ ሆስፒታሉ ለሕክምና ሲገቡ የተመለከቱ ሲሆን፤ ተኝተውበታል ተብሎ የሚጠበቀው ክፍል በፕሬዝዳንቱ አጃቢዎች ጥብቅ ጥበቃ እየተደረገለት ነው።
ስለሁኔታው የተጠየቁት በቤተመንግስት የሚገኙ ምንጮች ፕሬዝዳንቱ ከመታመማቸው በፊት ስብሰባ ሲመሩ እንደነበር በመጥቀስ ፤የከፋ ሕመም ሳይሆን ቀለል ያለ ህመም ታመው ታክመው እንደተመለሱ ቢገልፁም፤ ጋዜጣው ማተሚያ ቤት እስከገባበት ሰዓት ድረስ ግን ፕሬዝዳንቱ በኮሪያ ሆስፒታል እንደሚገኙ ከሆስፒታል ምንጮቹ ማረጋገጡን አመልክቷል።
ፕሬዝዳንት ግርማ፤ በመጪው ዓመት መስከረም ወር የሥልጣን ጊዜያቸውን አጠናቀው ከሥልጣን ይወርዳሉ ተብሎ ይጠበቃል
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide