በአርዱፍ ታግተው የቆዩት ሁለት ጀርመናውያን ተለቀቁ

የካቲት 28 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር(አርዱፍ) ታግተው የቆዩት ሁለት ጀርመናውያን ተለቀቁ።

አርዱፍ ባወጣው መግለጫ፤ ሁለቱን ጀርመናውያን ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ለ አፋር ሽማግሌዎችና በኢትዮጵያ ለጀርመን ኤምባሲ ባለሥልጣናት ማስረከቡን አስታውቋል።

ባለፈው ጥር ወር መግቢያ ላይ በአርዱፍ አማፅያንና በኢትዮጵያ መንግስት ታጣቂዎች መካከል  አፋር ውስጥ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የአርታሌ እሳተ ገሞራን ለመጎብኘት ወደ ሥፍራው ሲሄዱ የነበሩ አምስት የውጭ ቱሪስቶች መገደላቸውና ሁለት  መታገታቸው  ይታወሳል።

ከተገደሉት አምስት ቱሪስቶች ሁለቱ የጀርመን፣ሁለቱ የኦስትሪያና አንዱ የሀንጋሪ ዜጋዎች ሲሆኑ፤እስካሁን ድረስ ለግድያው ሀላፊነቱን የወሰደ አካል ወይም ቡድን የለም።

የኢትዮጵያ መንግስት  ቱሪስቶቹ የተገደሉት በአርዱፍ አማጽያን እንደሆነና ከግድያው ጀርባም የኤርትራ መንግስት እጅ እንዳለበት ሲናገር፤ አርዱፍ ባወጣው መግለጫ ደግሞ፦ ቱሪስቶቹ የተገደሉት በኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል።

ጥቃቱ በተፈፀመ ማግስት የኢትዮጵያ መንግስት  በአርዱፍ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ፤ ታግተው የቆዩትን ሁለት ጀርመናውያን በማስለቀቁ ሂደት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተጽዕኖ መፍጠሩ ታውቋል።

ሆኖም፤ የኢትዮጵያ መንግስት አቋም በታገቱት ቱሪስቶች ደህንነት ዙሪያ አደጋ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት በጀርመን መንግስት ጭምር በመፈጠሩ  ጉዳዩ ወደ ድርድርና ሽምግልና አምርቷል።

በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ  ትናንት በሰጠው መግለጫ ፤ የኤምባሲው ባለሥልጣናት ከአካባቢው የ አገር ሽማግሌዎች ጋር ባደረጉት ድርድር ታግተው  በአርዱፍ ታግተው የቆዩት ሁለቱ ጀርመናውያን ቱሪስቶች መለቀቃቸውን አስታውቋል።

የሁለቱ ጀርመናውያን መለቀቅ፤ “በአምስቱ ቱሪስቶች ላይ ግድያ የፈፀመው ማነው?” የሚለውንና- የኢትዮጵያ መንግስትና አማጽያኑ እየተወዛገቡበት ያለውን  ዋነኛ ጉዳይ በምርመራ ማጥራት ለሚፈልጉ ወገኖች የጎላ ጠቀሜታ እንደሞኖረው ይጠበቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide