የካቲት 21 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ባለፈው ቅዳሜ በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ህዝቡ በሚያስገርም ቁጣ ባለስልጣኖችን ስልጣን ልቀቁ በማለት በድፍረት ሲናገር እንደነበር ታወቀ አዲሱን የመሬት ሊዝ አዋጅ ለማወያየት በሚል ምክንያት በተጠራው ስብሰባ ህዝቡ ” እናንተ አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ባቆዩት አገር መሬት ሰጪና ነሺ ማን አደረጋችሁ፤ በሙስና የተጨማለቃችሁ መሆኑ እየታወቀ መሬት ለመሸጥ ምን የሞራል ብቃቱ አላችሁ፣ ህዝቡ በምርጫ 97 ወቅት አንፈልጋችሁም ብሎአል ለምን የባሰ ጊዜ ሳይመጣ ስልጣን አትለቁም፣ እናንተ እኛን አታስተዳድሩንም ” የሚል ይዘት ያለው ንግግር ሲናገሩ እንደነበር ዘጋቢያችን አጠናቅሮ የላከው ዘገባ ያመለክታል።
በህዝቡ እና በባለስልጣናት መካከል መግባባት ባለመደረሱና የህዝቡ ቁጣ ገንፍሎ በመውጣቱ በሁለት ቀበሌዎች ባለስልጣናቱ ስብሰባውን ሲበትኑ፣ በዋናው የመዘጋጃ ቤት አዳራሽ የተሰበሰበው ህዝብ ደግሞ ስብሰባውን ረግጦ ወጥቷል።
ከስብሰባው በሁዋላ ዘጋቢያችን በስልክ ያነጋገራቸው አቶ ተዘራ ይፍሩ የተባሉ የከተማው ነዋሪ እንደተናገሩት የቅዳሜው ሰልፍ ለመንግስት ባለስልጣናት ግልጽ የሆነ መልእክት ያስተላለፈበት ነበር ።
በንግግሩ መሀከል የኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ የተወገዘበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበርም አቶ ተዘራ ገልጠዋል በዚሁ ዞን በጪንጫ ወረዳ ደግሞ በቅርቡ የተፈጠረውን የሀይማኖት ግጭት ተከትሎ ከፌደራል እና ከክልሉ መንግስታት ተወክለው የመጡትን ባለስልጣናት አንቀበለም በማለት እንደመለሳቸው ታውቋል።
በዚሁ ወረዳ በቅርቡ አንድ የፖሊስ ባልደረባ ታቦት ለማንገስ በወጣው ህዝብ ላይ መተኮሱን እና አንድ ሰው ገድሎ 9 ማቁሰሉን መዘገባችን ይታወሳል።
ድርጊቱ የፈጠረው ውጥረት ሳይበርድ ደግሞ አንድ ቤተክርስቲያን መቃለጡ፣ የወረዳው ህዝብ በባለስልጣኖች ላይ ቂም እንዲቋጥር አድርጎት ቆይቷል። ሰሞኑን በአካባቢው ያለውን ውጥረት ለማብረድ የተላኩት ከፍተኛ ባለስልጣናት የወራደውን ሹም ጨምሮ ሶስት አመራሮችን ከስልጣን ማውረዳቸውን ቢናገሩም፣ ህዝቡ ግን የሚቀበለው አልሆነም። የህዝቡ አቋም ያስደነገጣቸው ባለስልጣናቱ ምንም አይነት የማስገደድ ስራ ሳይሰሩ ወደ መጡበት ተመልሰዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ዞን በካምባ ወረዳ የ2002 የምርጫ አስተባባሪ የነበረው እዝቅኤል የተባለ የመድረክ አባል ጸረ ሰላምና ጸረ ልማት ነው በሚል መታሰሩን ዘገባያችን አክሎ ገልጧል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide