የካቲት 21 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በህዝብ አመፅ ከስልጣን የተባረሩት የየመኑ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አሊ አብደላ ሳላህ በኢትዮጵያ ጥገኝነት የመጠየቅ ሃሳብ እንዳላቸዉ ረዳቶቻቸዉ ገለፁ
ጥቂት ዘመዶቻቸዉ እንዳደረጉት ሁሉ ኦማንን እና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስን ለመሳሰሉ አገሮች የጥገኝነት ጥያቄ ያቀርባሉ ተብለዉ ይጠረጠሩ የነበሩት የየመን የቀድሞ አምባገነን ፕሬዝዳንት አሊ አብደላ ሳላህ ለጥገኝነት ጥያቄያቸዉ የሚያስቧት አገር ኢትዮጵያ እንደሆነች ረዳቶቻቸዉ ገለፁ።
የመንን ለረዢም አመታት በአምባገነን የመሩት አሊ አብደላ ሳላህ በአገራቸዉ ዉስጥ የመኖር ፍላጎት ቢኖራቸዉም በዘላቂነት በየመን የሚኖሩ ከሆነ በደጋፊዎቻቸዉና በዘመዶቻቸዉ አማካይነት አዲስ ግጭት እንዲቀሰቀስ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስጋትና ጥርጣሬ አሳድሯል።
በመሆኑም ስልጣን በተረከቡት የቀድሞዉ ም/ፕሬዝዳንትና የአሁኑ ፕሬዝዳንት አብድራቡ መንሱር ሃዲ፤ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩን ባስፈፀሙት አለም አቀፍ ሸምጋዮችና በየመን ህዝብ በኩል የአሊ ሳላህ የመን ዉስጥ መኖር ተቀባይነት አላገኘም።
በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ መንግሰት ጋር በተደረገ ስምምነት መሰረት አሊ አብደላ ሳላህ በኢትዮጵያ በስደተኛነት እንደሚኖሩ ረዳቶቻቸዉ ገልፀዋል።
ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ የመኖሪያ ቪላ እንደተዘጋጀላቸዉና የቤት እቃዎቻቸዉ ወደ ኢትዮጵያ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።
የባህረ ሰላጤዉ አገሮችና የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩን በመሸምገል ስልጣናቸዉን እንዲያስረክቡና በምትኩ ያለመከሰስ መብት እንዲጠበቅላቸው መደገፋቸዉ ይታወቃል።
የፕሬዝዳንት ኦባማ የፀረ ሽብር አማካሪ ጆን ኦ ብራይን በሰንዓ በተገኙበት ወቅት “የሳላህ ወደ አገር መመለስ ማለት ሌላ ጦርነት መቀስቀስ ማለት ነዉ” በማለት ጠ/ሚር መሃመድ ማሳሰባቸዉ የሚታወቅ ሲሆን ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ የየመን ሰላምና መረጋጋት በሳዉዲ አረቢያ ባህረሰላጤ ከአልቃይዳ ጋር ለሚደረገዉ ዉጊያ ወሳኝ እንደሆነ ታምኖበታል።
በየመን በሁለት አመት ጊዜ ዉስጥ አዲስ ህገ መንግሰት እንደሚረቀቅና በህዝብ እንደሚፀድቅ፤ አዲስ የፓርላማና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚከናወን ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የፀረ ሳላህ ተቃዉሞ ንቅናቄ ቃል አቀባይ ከቀድሞዉ አምባገነን መሪ ምክትላቸዉ ወደነበሩት በተፈፀመዉ የስልጣን ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ ሳላህ በፈቃዳቸዉ ስልጣን አስረክበዉ የወረዱ ለማስመሰል የተደረገዉ ጥረት የየመንን ህዝብ ያስቆጣ ነበር ማለታቸዉን አሶስየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ገልጿል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide