ሱዳን ስደተኞችን አሳልፎ በመስጠት የሚፈፅመዉ ህገወጥ ተግባር ተወገዘ

የካቲት 21 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መሰረቱን በርሊን/ ጀርመን ያደረገዉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች የትብብር ኮሚቴ Solidarity Committee for Ethiopian Political Prisoners (SOCEPP) የሱዳን መንግስት በአገሩ የሚገኙ የፖለቲካ ስደተኞችን አሰገድዶ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በተጠናከረ ሁኔታ በመፈፀም ላይ ያለዉ ተግባር አለም አቀፍ ድንጋጌን የሚጥስ መሆኑን መግለፁን ኦል አፍሪካን ኒዉስ ዘገበ።

የሱዳን መንግስት ፖሊሶች ዋና ከተማዋን ካርቱምን ጨምሮ በኡምዱርማንና በሌሎችም ከተሞች በመኖሪያ ቤቶች አሰሳና ከበባ በማድረግ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን አድኖ በመያዝ በሃይል ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ላይ መሆኑን የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ገልጿል።

በአሰሳና በከበባ የሰበሰባቸዉን ኢትዮጵያዉያን ስደተኞ የጫነ ተሽከርካሪ ተገልብጦ 42 ስደተኞችና ሁለት የሱዳን ፖሊሶች መሞታቸዉን የገለፀዉ ኮሚቴ ፣ የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ለጉዳዩ ጀርባዉን መስጠቱና በጠቅላላዉ በሱዳን በተለያዩ እስር ቤቶች ዉስጥ በመሰቃየት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን መብት ለማስከበር ባለመቻሉ የተሰማዉን ቁጣ ገልጿል።

ኮሚቴዉ ለሱዳን ትሪቡን  በላከዉ መልእክት “ የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽንና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ተንከባካቢ ድርጅቶች የሱዳን መንግሰት በመፈፀም ላይ ያለዉን ህገ ወጥ ተግባር እስካልተቃወሙ ድረስ ሱዳን በስደተኞቹ መብት ላይ የምታደርሰዉ ጥሰት በማን አለብኝነት እንደሚቀጥል አመልክቷል።   

ከዚህ ቀደም ሱዳን አሳልፋ የሰጠችዉ አዛናዉ ደምሌ የተባለዉ ኢትዮጵያዊ ስደተኛን የመለስ መንግስት የት እንዳደረሰዉ እንደማይታወቅና አለም አቀፉ ህብረተሰብም ምንም አይነት ተቃዉሞ እንዳላቀረበ በመግለፅ ስደተኞቹ ተላልፈዉ ከተሰጡ አደጋ ሊደርስባቸዉ እንደሚችል ገልጿል። 

የጄኔቫዉን የስደተኞች ድንጋጌና የተባበሩት መንግስታትን የሰብኣዊ መብት ድንጋጌ በመጣስ ሱዳንና ኢትዮጵያ ድርጊቱን በመፈፀም ላይ የሚገኙት በጋራ ባደረጉት ልዩ ሰምምነት መሰረት መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች የትብብር ኮሚቴ አስታዉቋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፈዉ አመት አንዱአለም አለማየሁ የተባለዉን በኤርትራ በኩል የገባ የፖለቲካ ተቃዋሚ በአስመራ ሬዲዮና ቴሌቪዢን በኢትዮጵያ መንግሰት ላይ የሰላ ሂስ ይሰነዝር የነበረን ከታሰረበት የካርቱም ማእከላዊ ኮበር እስር ቤት የሱዳን ባለስልጣኖች አሳልፈዉ መስጠታቸዉን ድርጅቱ አስታዉሷል። 

የሱዳን መንግሰት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ስምምነት እያለዉ ባለፈዉ አመት ቁጥራቸዉ 361 የሆነ የኤርትራ ስደተኞችን ለኤርትራ መንግስት አሳልፎ መስጠቱ ይታወሳል።

በኦምዱርማን 12 ሺ ኢትዮጵያውያን መታሰራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide