የካቲት 3 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የሶሪያ የመከላከያ ሆስፒታል አዛዥ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል ዶ/ር ኢሳ አል ኮሊ የተገደሉት በታጠቁ አሸባሪዎች ነው ሲሉ የመንግስቱ የመገናኛ ኤጀንሲ ዘግቧል።
በሶሪያ ህዝባዊ አመጽ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አንድ ከፍተኛ የወታደራዊ አዛዥ ሲገደሉ ብርጋዴር ጄኔራል ዶ/ር ኢሳ አል ኮሊ የመጀመሪያ ናቸው።
የሶሪያ መንግስት ወታደሮች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሆምስ በከፈቱት ጥቃት ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የመገናኛ ብዙሀን እየዘገቡ ነው።
የአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ባለፈው አመት በአገሪቱ አመጽ ከተነሳ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ7 ሺ በላይ ሶሪያውያን ተገድለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት የሆኑት ሩሲያና ቻይና በምእራባዊያን እና በአንዳንድ የአረብ አገራት ተረቆ የቀረበውን ፕሬዚዳንት በሽር አላሳድ ስልጣናቸውን ለምክትላቸው እንዲሰጡ የሚጠይቀውን ረቂቅ ሀሳብ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ሰኡዲ አረብያ የጸጥታው ምክር ቤት ውድቅ ካደረገው ረቂቅ ጋር የሚመሳሰል ሌላ ረቂቅ በማዘጋጀት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲወያይበት ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምራለች።
በሶሪያ የሚካሄደው ተቃውሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሊቢያን አይነት ቅርጽ እየያዘ መምጣቱ ይነገራል።
አንዳንድ ወገኖች ፕሬዚዳንት በሸር አልአሳድ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ ስልጣናቸው ይለቃሉ በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።