የኢትዮጵያ መንግስት በሳውዲ አረቢያ ለታሰሩ ወገኖቻቸው በቂ ትኩረት አልሰጠም ተባለ

የካቲት 3 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢንተርናሽናል ክርስቲያን ኮንሰርን ባወጣው ዘገባ እንዳመለከተው፣ በእስር ላይ የሚገኙት 35 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉላቸው ቢጠይቁም፣ የኢምባሲው ሰራተኞች ግን ለጉዳያቸው ትኩረት ሊሰጡ አልፈለጉም።

እስረኞቹ እንደሚሉት አንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በጎበኛቸው ወቅት በአራት ቀናት ውስጥ ተመልሶ እንደሚመጣ ቃል ቢገባላቸውም ፣ እስከ ዛሬ ዘወር ብሎ እንዳላያቸው ተናግረዋል።

በጂዳ ኢምባሲ ጽህፈት ቤት ሰራተኛ  የሆኑት መርዋን በድሪ፣ ወንድ እስረኞችን በእስር ቤት ተገኝተው እንደጠየቁዋቸው ተናግረዋል።

እስረኞቹ ግን ወኪሉ ችግራቸውን ለመስማት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ፣ እንዲያውም  ስልክ እንደዘጉባቸው ተናግረዋል።

የኢንተርናሽናል ክርስቲያን ኮንሰርን ሀላፊ የሆኑት ጆናታን ራኮ ሲናገሩ ፡ የአንድ ዲፕሎማት ስራ የአገሩን ዜጎች መንከባከብ ነው። በዚህ ረገድ በጂዳ የሚገኙ የኢትዮጵያ  ልኡካን ሀላፊነታቸውን አልተወጡም። የእሰረኞችን ችግር ለመስማት እንኳ ፈቃደኞች አይደሉም። ማንኛውም ጉዳዩ ያገባኛል የሚል ወገን ሁሉ ክርስቲያኖቹ እንዲፈቱ ግፊት ማድረግ አለበት” ብለዋል።

የሳውዲ አረብያ መንግስት 35 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ያሰረው ፣ ሴቶችና ወንዶች በአንድ ላይ ተቀላቅለው አምልከዋል በሚል ምክንያት ነው።

በሳውዲ አረብያ  የቅርብ ቤተሰቦች ያልሆኑ ሴቶችና ወንዶች በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲገኙ አይፈቀድም። ሳውዲ አረብያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር እየፈጠረች የምትገኝ አገር ናት።

ሼክ ሙሀመድ አላሙዲ በጋምቤላ ክልል የሚያመርቱት ሩዝ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው ለሳውዲ አረብያ ገበያ የሚቀርብ ነው። ሳወዲ አረብያ ኢትዮጵያ ለአገሩዋ አስተማማኝ የግብርና ምርት አቅራቢ ለማድረግ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መመደቡዋ ይታወቃል።