ጥር 29 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቤት ሰራተኛነት የስራ ኮንትራት ፈፅማ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ አቡ-ዳቢ ከገባች ከሁለት ቀን በሁዋላ በተሰማት ህመም ወደ ሆስፒታል ስትወሰድ የ9 ወር ነፍሰ ጡር ሆና በመገኘቷ የወሊድ አገልግሎት የተሰጣት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ የሆስፒታሉን እዳ እስካልከፈለች ድረስ እንደማትለቀቅ ገልፍ ኒዉስ የዜና ምንጭ ገለፀ።
ስፖንሰር አድራጊዋና አስቀጣሪ ድርጅቷ ስለ እርግዝናዋ ምንም እንደማያዉቁና ተሰማኝ ባለችዉ የሆድ ህመም ምክንያት በስፖንሰርዋ አማካይነት አል ራህባ ሆስፒታል ተወስዳ እርግዝና መሆኑ ተረጋግጦ እንድትገላገል መደረጓ ታዉቋል።
ከሆስፒታሉ በተገኘዉ መረጃ መሰረት ሆስፒታሉ ለማዋለድ ለሰጠዉ አገልግሎት የሚፈለግባትን ክፍያ እስካልፈፀመች ድረስ እንደማያስወጣት ገልጿል።
በሌላ በኩል በአቡ ዳቢ የነዋሪዎችና የዉጭ ዜጎች ጉዳይ መንግስታዊ ጽ/ቤት ዉስጥ የስራ ሃላፊ የሆኑ ሰዉ የኢትዮጵያዊቷ ቪዛ እንደሚሰረዝና ለእድሜ ልክ ወደ ተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እንዳትገባ የሚደረግ መሆኑን ለገልፍ የዜና ምንጭ ገልፀዋል።