ጥር 29 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት ኢሳትን ለማፈን ሙከራ አድርጎ ከአረብ ሳት እንዲወርድ ካደረገው በሁዋላ በተመሳሳይ እርምጃ የኤርትራን ቴሌቪዥን ለማፈን ባደረገው ሙከራ በአረብ ሳት የሚተላለፈው ዝግጀቱ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወቃል።
አረብ ሳት ለኢትዮጵያ መንግስት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ቢቆይም፣ በማፈን ተግባሩ የቀጠለው መንግስት በአረብ ሳት የሚተላለፈው ዝግጀቱ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
የኤርትራ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ የሚያስተላልፈው ስርጭቱ እስከ ዛሬ ሳይታፈን ቆይቶ አሁን ለመታፈን ያበቃው፣ አንዳንድ ዝግጅቶችን ከኢሳት ድረገጽ ላይ እየወሰደ ማቅረብ በመጀመሩ ነው የሚሉ አስተያየቶች ይሰማሉ።
የአርቲስት ታማኝ በየነ እና የዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ንግግሮች እንዲሁም በአርቲስት እያሱ በርሄ አሟሟት ዙሪያ የተሰራው ቪዲዮ በኤርትራ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ መቅረብ ፣ የኢትዮጵያን መንግስት እንደረበሸውና ለአፈና እንዳነሳሳው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ ።
በሌላ በኩል የኤርትራ መንግስት በአረብ ሳት የሚያስተላልፈው ስርጭት በአፈናው ምክንያት ቢቋረጥበትም፣ በናይል ሳት ዝግጅቱን እያስተላለፈ መሆኑ ታውቋል።
ኢሳት በአጭር ሞገድና በቴሌቪዥን የሬዲዮ ስርጭት ወደ ኢትዮጵያ በማስተላለፍ ላይ ይገኛል።
ኢሳት ቴሌቪዝንን ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ በቅርቡም ስርጭቱ ይጀመራል የሚል ተስፋ መኖሩን ማኔጂመንቱ ገልጧል።