በጋምቤላ ክልል ያለው ውጥረት በሳምንቱ መጨረሻም አይሎ ነበር ተባለ

ጥር 28 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የክልሉ ዘጋቢያችን እንደገለጠው  በምስጢር የደኅንነት አባል ሆነው ሢሰሩ  የነበሩት   አቶ ጌታቸው አንኮሬ  ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ  ጋምቤላ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናትና ዛሬ በመከላከያ ሰራዊት እና በፌደራል ፖሊስ አባላት ዙሪያዋን ታጥራለች።

ትናንት የፌደራል ሰራዊት አባላት በየአቅጣጫው ውጠራ አድረገው አላፊ አግዳሚውን ሲፈትሹ እንደነበር የገለጠው ዘጋቢያችን፣ በከተማው ነዋሪ ላይም ከፍተኛ የሆነ አለመረጋጋት ይታያል።

የአካባቢው ባለስልጣናት በከፍተኛ ፍርሀት ውስጥ በመግባታቸው እርስ በርስ እስከመጋጨት መደረሳቸውም ታውቋል።

አቶ ጌታቸውን የክልሉ ባለስልጣናት ራሳቸው እንዳስገደሉዋቸው ጥርጣሬ መኖሩን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጧል። ከእርሳቸው ግድያ ጋር በተያያዘም 5 ሰዎችን ታስረዋል። አቶ ጌታቸው በአቦቦ አካባቢ እጅግ ሰፊ የሆነ መሬት እንዳላቸው እና በስልጣን መባለግ የታወቁ እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል።

የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ አባላት በከተማው ውስጥ ጸጉረ ልውጦች ገብተዋል በማለት ፍተሻ እያካሄዱ ቢሆንም፣ የክልሉ ምክር ቤት ግን እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።

አምሽቶ መግባት፣ ወደ መዝናኛ ቦታዎች መሄድ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው የሚለው ዘጋቢያችን፣ የክልሉ ባለስልጣኖች ሳይቀር በከፍተኛ ስጋት ውስጥ በመውደቃቸው በአካባቢው እንደልባቸው ሲንቀሳቀሱ አይታይም።

የጸጥታው መደፍረስ ዋነኛ ምክንያት የአካባቢው ህዝብ ያለፍላጎቱ በሰፈራ መርሀግብር እንዲፈናቀል መደረጉ መሆኑን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጧል።