ጥር 15 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በደቡብ ክልል በአዋሳ ከተማ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ግዳጃቸዉን ፈጽመዉ በክብር የተሰናበቱ ተራ ወታደሮች ወደ ትውልድ ስፍራቸዉ ተመልሰዉ የቤት መስሪያ ቦታ ወይንም የኮንዶሚኒየም ቤት ለመግዛት ቅድሚያ እንዲሰጣቸዉ ያቀረቡት ጥያቄ በክልሉ ባለስልጣናት ተቀባይነት ማጣቱን በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በሰፈረ ብሶት ተገለፀ።
የክልሉ መስተዳድር፤ የክልሉ ቤቶች የልማት ኤጀንሲ፤ የቤቶች ልማት ቦርድ የወታደሮቹን ጥያቄ ዉድቅ አድርገዉ በምትኩ የኮንዶሚኒየሙ ቤት ግዢ ክፍያ በመከላከያ ሚኒስቴር ለሚፈፀምላቸዉ ከፍተኛ መኮንኖች ቅድሚያ መሰጠቱ ተገልጿል።
በክልሉ በመገንባት ላይ የሚገኙት የኮንዶሚኒየም ቤቶች በዕጣ ይከፋፈላሉ እስከተባለ ድረስ በመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን በተፃፈ ደብዳቤ ለመኮንኖቹ ቅድሚያ ከመሰጠቱም በላይ
ለመኮንኖቹ ቤት ግዢ ሙሉ ክፍያውን መንግሥት እንዲከፍልላቸው መደረጉ አጠያያቂ መሆኑን አመልክቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጋዜጣዉ ላይ የቀረበዉ ቅሬታ በቁርጥ ቀን የአገሩን ጥሪ ተቀብሎ በመዉጣት የተማገደው ምስኪን ወጣት የሚፈለገዉ ለጦርነት ብቻ መሆኑን ጠይቋል።
ይህ በሃዋሳ የአገር መከላከያ ግዳጃቸዉን በፈፀሙ ተመላሾች ላይ ተፈፀመ የተባለዉ አድልዎ በአገሪቱ ዉስጥ እየተንሰራፋ በመሄድ ላይ ካለዉ የገዢዉ ፓርቲ ወገናዊነት፤ ሙስና ወይንም ሌላ ምክንያት የመነጨ መሆኑን ለማወቅ አልተቻለም።
አሰራሩ አሁን ወታደራዊ ግዳጃቸዉን በመወጣት ላይ ባሉ የሰራዊቱ ተራ ወታደሮችና ወደፊትም የአገር አንድነትን ለማስከበር ከሚጠበቀዉ የሙያ ግዴታ አንፃር ሊያስከትል የሚችለዉ ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ መገመት አያዳግትም።