የእስራኤል ፕሬዝዳንት ለኢትዮጵያዊያን ቤተ እስራኤላዉያን የዘፈን ግጥም ደረሱ

ጥር 15 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-ኢትዮጵያዊ  ቤተ እስራኤላዉያን ላይ የደረሰዉ የዘር መድልዎ የተሰማቸዉ የእስራኤል ፕሬዝዳንት ሺሞን ፔሬዝ አንድ የዘፈን ግጥም በመድረስ እዉቁ የእስራኤል የዜማ ደራሲ እንዲያቀናብረዉ ማድረጋቸዉን አንድ የእስራኤል ጋዜጣ ገለፀ።

ፕሬዝዳንቱ ግጥሙን ያዘጋጁት በቅርቡ በእየሩሳሌም በሚገኝ ትምህርት ቤት ዉስጥ ባደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያዊያን ሕፃናት እስራኤላዊ ከሆኑ የህብረተሰቡ ህፃናት ጋር ያላቸዉ የቅርብ ትስስርና ዉህደት በመመልከታቸዉ ነዉ።

በተለይም የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነች ራሔል የተባለች ኢትዮጵያዊት  ዘማሪ  “ አቤት! እየሩሳሌም አንቺን ከረሳሁሽ..” በተሰኘ መዝሙር መድረኩን ስትመራ መመልከታቸዉ እጅግ ስለመሰጣቸዉ እንደሆነ ተናግረዋል።  

“ የራሄልን ዉብና ሩህሩህ ዓይኖች ልረሳቸዉ አልችልም፡ በዓይኖቿ ዉስጥ ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላዉያን ወደ እስራኤል ምድር ለመምጣት የደረሰባቸዉን መከራና የነበራቸዉን ፍላጎት ተመልክቻለሁ” ብለዋል። 

ከ5 ቀናት በሁዋላ የተቀናበረዉን መዝሙር ፕሬዝዳንት ፔሬዝ በእየሩሳሌም አለም አቀፍ የስብሰባ ማእከል በመገኘት ከማዳመጣቸዉም በላይ ከተቀመጡበት ተጋብዘዉ በመነሳት አብረዉ መዘመራቸዉ ታዉቋል።  

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያዊያን ቤተ እስራኤላዉያን በትምህርት ደረጃቸዉ የኮሌጅ የዲግሪ ምሩቅ ቢሆኑም ቅሉ በተመሳሳይ የስራ መደብ ላይ የሚያገለግሉ የእስራኤል ተወላጆች ከሚከፈላቸዉ ደመወዝ በግማሽ ያነሰ እንደሚከፈላቸዉ አንድ ጥናት አረጋገጠ።

የአገሪቱ የኢምግሬሽን መ/ቤት በኢንስቲትዩት ያስጠናዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ በእስራኤል 20 አመትና ከዚያ በላይ የቆዩት ኢትዮጵያን ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ከተወላጆቹ ጋር ሲነፃፀር የሚያገኙት ክፍያ በግማሽ ዝቅ እንደሚል ተገልጿል። 

ከክፍያዉ አነስተኛ መሆን ባሻገር አብዛኛዎቹ የሚሰሩበት የሙያ መስክ ከተማሩት የትምህርት መስክ ጋር እንደማይጣጣም በተጨማሪ ለማወቅ መቻሉን ሃርትዝ የዜና ምንጭ አመልክቷል።