ጥር 14 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት መንግሥት በነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በአሸባሪነት ወንጀል በከሰሳቸው የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት፣ ጋዜጠኞች እና ነፃ አሳቢ ዜጎች ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ብይን የመስጠት ሂደቱን በጊዜ አሻገረ፡፡
ዛሬ ጠዋት 3፡00 ሰዓት ላይ የነ አንዷለም አራጌን የክስ መዝገብ ተመልክቶ የጥፋተኝነት ወይም ከጥፋት ነፃ የመሆን ብይን ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት እጅግ ዘግይቱ ከቀኑ 5፡30 ሰዓት ላይ የተጀመረ ሲሆን፤ የመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ ” ከዚህ ቀደም በንባብ ተጠናቆ ወደ ጽሑፍ ተገልብጦ ያልቀረበልኝ የዐቃቤ-ሕግ የድምጽና የምስል ማስረጃ በጽ/ቤት በኩል ቢቀርብልኝም ፤ገና መርምሬ ባለማጠናቀቄ ለዛሬም ብይን መስጠት አልቻልኩም” ብለዋል፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ አቤቱታ አለኝ በማለት ፍርድ ቤቱን በመጠየቅ፦ ”ፍርድ ቤቱ የእኛንም ሁኔታ በእኩል የፍትህ ዐይን የሚያስተናግደን ከሆነ ፤ከመጀመሪያ ጀምሮ ገና በፍርድ ቤት እየተከራከርንበት ባለው ሁኔታ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ራዲዮ ድርጅት (ኢቲቪ) አኪልዳማ በሚል በሰራው ፕሮፓጋንዳ ወንጀለኛ አድርጎ ሲያቀርበን ፍርድ ቤቱ እርምጃ ባለመውሰዱ የተነሳ፤ ይኸው በትላንትናው እለትም ሌላ የፕሮፓጋንዳ ዶኩመንተሪ ሰርቶ አቅርቦብናል፣ እ ባካችሁ ስለፍትህ ስትሉ አስቁሙልን‘ ተማጽኖ አቅርቧል ፡፡
የመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ ግራ ቀኝ ተነጋግረው “አቤቱታ ያላችሁ አቤቱታችሁን በጽሑፍ በጽ/ቤት ማቅረብ ትችላላችሁ አሊያም ነገ ብይን ሰጥተን ስናጠናቅቅ ማቅረብ ትችላላችሁ” በማለት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
በዳኞቹ ውሳኔ ቅር የተሰኘው አቶ አንዷለም አራጌ ”ከመጀመሪያ ጀምሮ ፍርድ ቤቱ እኛ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ኢፍትሃዊ በደልና ሰቆቃ እየተመለከተ አይደለም … ‘ በማለት ሲናገር የመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ ”አንደኛ ተከሳሽ! ሁሉ ነገር ሥርዓት አለው፣ በዚያ ነው የሚሄደው አቤቱታችሁን ነገ ከብይን በኋላ ታቀርባላችሁ‘ በማለች ችሎቱ ለ ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ቀጠሮ ሰጥቶ ተበትኖአል።