ጥር 14 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በሶማሊ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በደረሰባቸው የሀይል ጥቃት የተነሳ ወደ ኦሮሚያ ክልል መሰደዳቸውን የገለጡ 80 ሺ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ በቂ የሆነ የምግብ እርዳታ ስላልቀረበላቸው በቀን አራትና አምስት ሰዎች እየሞቱባቸው እንደሆነ ተናገሩ።
ቁጥራቸው ከ300 ሺሕ በላይ የሆነውና በሶማሌ ክልል ይኖሩ የነበሩት የፊቅ ዑመር ወይም የሸካሽ ጎሳ ማኅበረሰብ አባላት በቂ እህልና ውሀ እንዲቀርብላቸው በተደጋጋሚ መንግስትን ሲጠይቁ ቆይተዋል።
የማህበረሰቡ አባላት የክልሉ መንግሥት በእኩል እንደማያቸው፣ የማንነት መብታቸውን እንደተነፈጉና ከማናቸውም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ተገለናል በማለት አቤቱታ ሲያሰሙ እንደቆዩም የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል።
የማኅበረሰቡ ተወካይ የሆኑት አቶ መሐመድ አብዱላሂ ለጋዜጣው እንደገለጹት፣ የክልሉ መንግሥትና የፀጥታ ኃይሎች በጎሳው ላይ የኃይል ጥቃት በመፈጸም፣ አቤቱታ የሚያቀርቡ ተወካዮቻቸውን ለእስርና ለድብደባ ይዳርጋሉ፡፡
የማኅበረሰቡ አባላት” ራሶ” በተባለ የአፋር ክልል ተጠልለው ከቆዩ በኋላ፣ መስከረም 15 ቀን 2004 ዓ.ም ወደ 80 ሺሕ የሚጠጉ የጎሳ አባላት ወደ ኦሮሚያ ክልል በመሸሽ ልዩ ስሙ “ሬቱ ወረዳ “በተባለው አካባቢ መስፈራቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
የማኅበረሰቡ አባላት ተወካዮች የክልሉ መንግሥት እርዳታ እንዳይደርሳቸው በመከልከሉ፣ በቀን አራትና አምስት ሕፃናትና አዛውንቶች ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መንግስት ጉዳዩን እንዲያጣራ የላከው አጣሪ ቡድን የብሄረሰቡን መፈናቀል አምኖ፣ እስካሁን የሞተ ሰው የለም ብሎአል።
ይሁን እንጅ እርዳታ ፈጥኖ ካልደረሰ በርካታ ህዝብ ሊያልቅ እንደሚችል አስጠንቅቋል።