“የሰብኣዊ መብት ሁኔታና ኢትዮጵያ የምትጫወተዉ አፍራሽ ሚና “ በሚል ርዕስ በለንደን ኮንፈረንስ ተካሄደ

ጥር 14 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:- “እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ያለዉ የምስራቅ አፍሪቃ የሰብኣዊ መብት ሁኔታና ኢትዮጵያ የምትጫወተዉ አፍራሽ ሚና “ በሚል ርዕስ በለንደን ኮንፈረንስ ተካሄደ

በምስራቅ አፍሪቃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ ይበልጥ እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ባለዉ የሰብኣዊ መብት ሁኔታና በተለይም በኢትዮጵያ የሚገኘዉ የጠ/ሚር መለስ ዜናዊ መንግሰት የሚከተለዉ የተሳሳተ አቅጣጫ በአፍሪቃ ቀንድ ያለዉን ችግር እንዳወሳሰበው በስብሰባው ተገልጧል።

በለንደን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የስብሰባ አዳራሽ ዉስጥ ቅዳሜ ጥር 12 2004 የተካሄደዉን ኮንፈረንስ ያዘጋጀዉ የኦጋዴን ሶማሌ የሰብኣዊ መብት ተንከባካቢ ቡድን ሲሆን በስብሰባዉ ላይ ቁጥራቸዉ ከ100 የማያንስ ኢትዮጵያዊያንና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል።

ስብሰባዉን ያስተባበሩትና በንግግር የከፈቱት አቶ መሃመድ ሼክ በርስ በርስ ግጭት፤በረሃብና በሰላም እጦት ያለማቋረጥ በሚታመሰዉ የአፍሪቃ ቀንድ ዉስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መንግሰት በየጊዜዉ የሚፈፅመዉ የሰብኣዊ መብት ጥሰት አካባቢዉን የስጋት ቀጣና እንዳደረገዉ አመልክተዋል።

በስብሰባዉ ላይ በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች፤ በቪዲዮና በፎቶ ግራፍ የቀረቡ ማስረጃዎች ቀርበዋል።

የሰብኣዊ መብት ገፅታዎች በኢትዮጵያ -በሚል ርዕስ በለንደን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች በሆኑት አቶ ዘለዓለም ተሰማ፣ “የአፍሪቃ ቀንድ የስደተኞች ሁኔታና ልምድ “- በሚል – በዶ/ር ትሬቨር ትሩማን፣ “የኢኮኖሚ ልማት ፕሮጀክቶችና የመልካም አስተዳደር እጦት በኢትዮጵያ” በሚል በአቶ አቻሜ ሻና፣  “በጋምቤላ የማህበረሰብን ህይወት አደጋ ዉስጥ የጣለ የመሬት ቅርምትና የመንደር ምስረታ”-በሚል  በአቶ ኒክዎ ኦቻላ ፣እና “የመሬት ቅርምት – ልማት ወይስ የጭቆና መሳሪያ” በሚል ርዕስ  በዳኛ ተሻለ አበራ ጽሁፎች ቀርበዋል።

የሰብሰባዉ ተካፋዮች ከዚህ በተጨማሪ በሶስት ምድብ ተከፍለዉ የሰብኣዊ መብት ጉዳዮችን በተመለከተ ሊኖር ስለሚገባዉ የተሳትፎና የትብብር አስፈላጊነት፤ በሰብኣዊ መብት ጉዳይ ላይ ሊወሰዱ ስለሚገቡ አዳዲስ የቅስቀሳና የዘመቻ ስራዎች እንዲሁም በቀጣይነት መወሰድ ስለሚኖርባቸዉ እርምጃዎች ተወያይተዋል።

የመለስ ዜናዊ መንግስት የሚፈፅማቸዉን የሰብኣዊ መብት ረገጣዎች ባለማሰለስ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ የማጋለጡ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፤ በለንደን የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ከያካባቢዉ ከሚገኘዉ የፖርላማ አባልና ከአለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለሚፈጥርበትና ከሁሉም በላይ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸዉ ወገኖች በየራሳቸዉ የግል አጀንዳ ዙሪያ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባሻገር ሁሉንም በጋራ በሚያስተባብር የተጠናከረ የህብረት እንቅስቃሴ ላይ ማተኮር ጠቃሚ እንደሆነ በኮንፈረንሱ  መጠቀሱን ንጉሴ ጋማ ከለንደን ዘግቧል።