ጥር 12 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል ብሎአል። የአለማቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው መንግስት አሁንም የተረጂዎችን ቁጥር ቀንሶ አቅርቧል ይላሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት ያወጣው ቅድመ ማስጠንቀቂያ አሀዝ እንደሚያሳየው በመጪዎቹ ስድስት ወራት ከ365 ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ አብዛኛው በኦሮሚያ እና በሶማሊ ክልሎች የሚከፋፋል ነው ብሎአል።
ከተረጅዎች ውስጥ 34 በመቶው በሶማሊ ፣ 33 በመቶ ደግሞ በኦሮሚያ እንደሚገኙ ታውቋል። ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የተረጅዎች ቁጥር በነበረው የትግራይ ክልል በአሁኑ ጊዜ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሎአል። በአማራ ክልል ደግሞ በፊት ከነበረው የተረጅዎች ቁጥር ጋር ሲተያይ በአሁኑ መረጃ ብዙም ለውጥ አልታየም።
የኦሮሚያ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ በድርቅ እየተጠቃ እና የተረጅዎች ቁጥር እጨመረ መምጣቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን የረሀብ ተጠቂ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እየቀየረው መምጣቱን የሚያመልክት መሆኑን መረጃውን ያቀበሉት የግብርና ባለሙያ ተናግረዋል።
በግብርና ምርቶች ዋጋ ጭማሪ ሲታይ ደቡብ ክልል ፣ ኦሮሚያና ሶማሊ ከአንድ እስከ ሶስት ያሉት ደረጃዎችን መያዛቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። የምግብ ዋጋ አነስተኛ ጭማሪ የታየ ሲሆን፣ በአዲስ አበባም ጭማሪው ቢኖርም እንደ ደቡብና ኦሮሚያ የከፋ አይደለም።
ኢትዮጵያ መንግስት አዲስ ያቀረበው የተረጅዎች ቁጥር የአለማቀፍ የግብረሰናይ ድርጅቶች እንዳልተቀበሉት ተውቋል። የኢትዮጵያ መንግስት 11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ፕሮፓጋንዳ የበርካታ ንጹሀን ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ እየጣለው ነው።
ሴቭ ዘ ችልደርንና ኦክስፋም ባወጡት መረጃ የኢትዮጵያ መንግስት በረሀብ የተጎዱ ዜጎቹን አሀዝ አሳንሶ በማቅረቡ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት አልፎአል ሲሉ በዚህ ሳምንት ባወጡት መግለጫ መተቸታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሶማሊ ባለፈው አመት በተከሰተው ረሀብ ከ50 እስከ 100 ሺ የሚጠጋ ህዝብ ማለቁን ድርጅቶቹ አስታውቀዋል።
የመለስ መንግስት ከአምስት አመታት በፊት ረሀብ ታሪክ ይሆናል፣ ከ17 አመታት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሶስት ጊዜ እንዲበላ እናደርገዋለን ማለቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጅ ለኢሳት የሚደርሱት መረጃዎች እንደሚያሳ ት በደቡብ፣ በኦሮሚያና በሶማሊ አሁንም ከፍተኛ ረሀብ ገብቷል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በአለም ባንክንና በሌሎችም ለጋሽ ድርጅቶች በሚሰፈርላቸው ስንዴ ብቻ የሚኖሩ ፣ ሴፍቲኔት በሚባለው ፕሮግራም የታቀፉ 7 ሚሊዮን ዜጎች አሉ።