ጥር 10 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማበወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ጊዜ የኤርትራ መንግስት የሚያካሂዳቸውን የሽብር ድርጊቶችና ለአሸባሪዎች የሚሰጠውን እርዳታ መታገስ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡፡
የኤርትራ መንግስት ያሰማራቸውአሸባሪዎች በአፋር ክልል የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን በመጎበኘት ላይ በነበሩ 27 ቱሪስቶች ላይ ከትናንትበስቲያ ጥቃት ማድረሳቸውንና አምስቱ መገደላቸውን ሚኒስቴሩ አስታውሷል።
የሽብር ጥቃቱ ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለማጨናገፍ ታቅዶ የነበረውን የሽብር ሴራ የሚያስታውስ መሆኑን መግለቻው ያስታውሳል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኤርትራመንግስት ላይ የማያዳግም ርምጃ ካልወሰደ የኢትዮጵያ መንግስትአስመራ ውስጥ ያለውን መንግስት የመከላከል ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል ሲል መንግስት ዝቷል።
የአፋር ህዝብ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ ኮንቲ ሙሳ በቱሪስቶች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የኢትዮጵያ መንግስት ሳይፈጽመው እንዳልቀረ አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል።
የኤርትራ የአፍሪካ ህብረት አምባሳደር የሆኑት ግርማ አስመሮም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በተካሄ ቁጥር እንዲህ አይነት ስሜት ኮርኳሪ የሆኑ ዜናዎችን መፍጠር ባህሪ አድርጋዋለች ማለታቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ ያሰማው ዛቻ የተለመደ ነው የሚሉ አስተያየቶችም ይቀርባሉ። አንድ አዲስ አበባ ያሉ ዲፕሎማት ድርጊቱ ምናልባትም የኢትዮጵያ መንግስት የአለማቀፉ ማህበረሰብ በኤርትራ ላይ ተጨማሪ ጫና እንዲያሳድር በማሰብ ራሱ ቱሪስቶችን ገድሎአቸው ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ዲፕሎማቱ የጥቃቱ ዜና እንደተሰማ የኢትዮጵያን መንግስት ምን ያክል ቱሪስቶች እንደተገደሉና ዜግነታቸው ከየት እንደሆነ ስንጠይቀው መረጃ የለኝም ብሎን ነበር፣ ነገር ግን ጥቃቱን የፈጸመው የኤርትራ መንግስት ያስታጠቃቸው አማጽያን ናቸው በማለት ነግሮናል። የሰዎችን ማንነት ማወቅ የተሳነው መንግስት በምን ያክል ፍጥነት በድርጊቱ የኤርትራ እጅ አለበት እንዳለ ለማወቅ አይቻልም ሲሉ በተዘዋዋሪ መንገድ የኢትዮጵያ እጅ ሊኖርበት እንደሚችል ጠቁመዋል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ በኩል ለሚሰነዘረው የጦርነት ዛቻ አንድም ቀን መልስ ሰጥታ አታውቅም። የኢትዮጵያ መንግስትም ኤርትራን እንደሚወጋ ከመዛት ተቆጥቦ አያውቅም ።