“የመኢአድ አባል የሆነ ሁሉ ይታሰራል እየተባለ ነው” ሲል መኢአድ ገለጸ

ጥር 10 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-በተለየ መልኩ በደቡብ ክልል በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) አባላት ላይ እየተፈፀመ ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየከፋ በመምጣቱ ፤  የዘንድሮ ጠቅላላ ጉባኤውን  እዚያው ክልል ውስጥ ለማድረግ መወሰኑን ፓርቲው አስታወቀ።

መኢአድ በመግለጫው እንዳለው፤ ጠቅላላ ጉባዔውን በክልሉ ማካሄድ ያስፈለገው፤ በክልሉ በሚገኙ የድርጅቱ አባላት ላይ ኢህአዴግ የሚያደርሰው ጭቆና እየበረታ በመምጣቱ፤ ጭቆናውን በህጋዊ መንገድ እንዴት መግታት እንደሚቻል ውሳኔ ለማሳለፍ ነው፡፡

በመሆኑም የዘንድሮው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ በደቡብ ክልል ጐፋ ሳውላ ከተማ ውስጥ  እንደሚያካሂድ ድርጅቱ አስታውቋል።

እንደ ድርጅቱ መግለጫ ከሆነ  በአሁኑ ጊዜ በደቡብ ክልል ውስጥ  በአባላቱ ላይ እየተፈፀመ ካለው አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ባሻገር፦‹‹የመኢአድ አባል የሆነ ሁሉ ተለቅሞ ይታሰራል›› የሚል ማስፈራሪያ  በአደባባይ ከኢህአዴግ አመራሮች እየተደመጠ ነው።

በክልሉ በዳሰነች ምርጫ ክልል ለተወካዮች ም/ቤት ተወዳድረው የነበሩት ወ/ሮ አማረች ገላኔ በ23

ጥይት ተደብድበው እንደተገደሉና የ10 እና 12 ዓመት ህፃናት ልጆቻቸው በጥይት እንደቆሰሉ ያወሳው  መኢአድ፤ባለቤታቸውም አቶ ጌልሄሎ ኩይታ ደግሞ ሀዘናቸውን በመግለፃቸው ብቻ  ስለት በያዙ ሰዎች ማስፈራሪያ እንደተፈፀመባቸው አመልክቷል።

የኢሳት ወኪል ከስፍራው ያደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው፦የ ኢህአዴግ ታጣቂዎች በአቶ ጌልሄሎ ላይ ማስፈራሪያ የፈጸሙት “ሚስትህም  ብትገደል፤ልጆችህም በጥይት ቢመቱ ሀዘንህን መግለጽ አልተፈቀደልህም። ሀዘንህን በሆድህ ውጠህ ዝም በል፤ አለበለዚያ ግን ዋጋህን ታገኛለህ!” በማለት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የመኢአድ አባላት እየተመረጡ ከመሬት ይዞታቸው  እና ከስራ ገበታቸው እየተፈናቀሉ መሆናቸውንም ፓርቲው አመልክቷል፡

አቶ ጴጥሮስ ወያኰ የተባሉ የመኢአድ አባል በአይዳልዩ ወረዳ ሰብሳቢ የተለያዩ ተክሎችን ሊያለሙበት የነበረ ቦታቸው ያለአግባብ ተወርሶ የግብርና ጽ/ቤት እንደተገነባበት በምሳሌነት የጠቀሰው መኢአድ፤ አቶ ጴጥሮስ ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ወስደው በማመልከት 21 ሺህ ብርና ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸው ቢወሰንላቸውም፣ የቀበሌው አመራሮች በግልጽ፦ ‹‹ከመኢአድ ካልወጣህ፤ መሬቱን አታገኝም!›› ብለው እንደከለክሏቸው ገልጿል።

ይሁንና፤  ይህ ሁሉ  ማስፈራሪያና ግፍ የፓርቲውን አባላት ከሰላማዊ ትግላቸው እንደማያደናቅፋቸው ገዥው ፓርቲ ሊረዳው ይገባል ሲል መኢአድ አስታውቋል።