ጥር 10 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሰሞኑን የ ኢጋድ አባል አገራት “ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት “ መፈራረማቸውን ተከትሎ በተለይ በ ኡጋንዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ከፍ ያለ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ገለጹ።
በአቶ መለስ መንግስት ግንባር ቀደም ፊታውራሪነት ሁሉም የኢጋድ አገሮች እንዲፈረም ግፊት እየተደረገበት ያለውና ሥራ ላይ ለመዋል ጥቂት ሳምንታት የቀረው ይህ ስምምነት ዋነኛ ዓላማው፤ በጎረቤት አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎችን “በወንጀለኛ ስም” ወደ አገራቸው መልሶ ለማሰቃየት እንደሆነ ታውቋል።
ይህን ሁኔታ የተገነዘቡ በተለይ በኡጋንዳ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የድረሱልን ጥሪ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
“የተመድ የስደተኞች ፅህፈት ቤት “ፕሮቴክሽን” እንዲሰጠን ወይም ለህይወታችን አስጊ ወዳልሆነ አገር እንዲያዛውረን በውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ፦ካምፓላ ወደ ሚገኘው የተመድ የስደተኞች ጽህፈት ቤትና ወደ ሰብአዊ መብት ተቋማት በተደራጀ መልኩ ደብዳቤና ፊርማ በመላክ ህይወታችንን ትታደጉን ዘንድ አደራ እንላለን” ሲሉ ኢትዮጵያውያኑ ተማጽነዋል።
በሱዳን በስደተኝነት ይኖር የነበረው አቶ አንዷለም ዓለማየሁ በቅርቡ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ እንደተሰጠና ከነ አንዷለም አራጌ ጋር የፈጠራ ሽብርተኝነት ክስ እንደተመሰረተበት መዘገባችን ይታወሳል።
“ተመሣሳይ አደጋ የተደቀነባቸውን በኡጋንዳ ያሉ ወገኖቻችንን በምንችለው አቅም ተሯሩጠን ልንታደጋቸው የምንችልበት ጊዜ አሁን ነው”ያሉ አንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ፤ “የኡጋንዳ መንግስት አሳልፎ ከሰጣቸውና ከታሰሩ በሁዋላ ፦”እስረኞች ይፈቱ!” እያልን ከመጮኽ ይልቅ፤ አሁን መስራት በምንችልበት ጊዜ ሰርተን ህይወታቸውን በማዳን ወያነን ብንቀድመው ነው አሸናፊዎች የምንሆነው” ብለዋል።