ጥር 7 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በሳኡዲ አረቢያ-ሪያድ ውስጥ የገናን በዓል ለማክበር በተሰበሰቡበት በፖሊስ ቁጥጥር ውለው ወደ አስፈሪ እስር ቤት ከተጋዙት 35 ኢትዮጵያውያን መካከል ሦስቱ በእስር ቤት ውስጥ መሞታቸውን በስፍራው የሚገኘው የኢሳት ወኪል ዘገበ።
ዘጋቢያችን እንዳረጋገጠው፤ የገናን በዓል ለማክበር በመሰብሰባቸው ሳቢያ ለ እስር ከተዳረጉት 35 ኢትዮጵያውያን መካከል፤ ህፃናት 29ኙ ሴቶች ናቸው።
ከነዚህ ሶቶች መካከል ብዙዎቹ የሚጠቡ ህፃናት ልጆቻቸውን በቤታቸው ትተው በዓሉን ለማክበር የመጡ ሲሆኑ፤ ለ እስር በመዳረጋቸው ከህፃናት ልጆቻቸው ጋር ከተለያዩ ፤በርካታ ቀናት እየተቆጠሩ ነው።
እንደ ዘጋቢያችን መረጃ ኢትዮጵያውያኑ የገናን በዓል ተሰባስበው እንዳያከብሩ የሳኡዲ ህግ አይከለክላቸውም ብቻ ሳይሆን፤ በአገሪቱ ህግ መሰረት የተፈቀደ ነው።
ኢትዮጵያውያኑ ሌሎች 400 እስረኞች ወደሚኖሩባትና ጠባብ ክፍል ውስጥ ለጤናቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ያለ በቂ ምግብ አቅርቦት እንዲታጎሩ መደረጋቸው የተመለከተ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ በሽታ ላይ መውደቃቸውና ከታመሙት መካከልም ሦስቱ መሞታቸው ታውቋል።
በጠባቡ እስር ቤት ውስጥ ለመተኛ የሚሆን በቂ ስፍራ ባለመኖሩም እስረኞቹ ቀንና ማታ እየተጠባበቁ በየተራ እንደሚተኙ ተገልጿል።
ከሁሉም የከፋው ደግሞ በፖሊሶቹ አማካይነት ባትዮጵያውያን ሴቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው አስነዋሪ ነገር ነው ይላል-የወኪላችን መረጃ፤ይሁንና በሴቶቹ ላይ ተፈፀመ ያለውን አስነዋሪና አሳዛኝ ነገር ለጊዜው ‘ለ ሶቶቹ ደህንነት”ሲል ከመግለጽ መቆጠብን መርጧል።
ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በሰብዓዊነት ላይ እየፈፀመ ያለውን ዘግናኝ ወንጀል እንዲያቆም ያስገድዱት ዘንድ በውጪ አገራት የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የስቃይና የመከራ ድምፃችንን ታሰሙልን ዘንድ እንማፀናለን”በማለት እስረኞቹ የድረሱልን ጥሪ ማቅረባቸውን የዘጋቢያችን መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያውያኑ የገናን በዓል ለማክበር መሰብሰባቸውን ተከትሎ ለእስር በመዳረጋቸው ዓለማቀፍ ብዙሀን መገናኛ ብዙሀን እየዘገቡ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት ፤በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምንም አለማለቱ ፤እንደተለመደው ብዙዎችን ያሳዘነ ሆኗል።
ይልቁንም ኤምባሲው ኢትዮጵያውያኑ በዚህ መከራ ውስጥ በወደቁበት ጊዜ-ላይ ታች እያለ ያለው፤ ለህዳሴው ግድብ ገንዘብ ለመሰብሰብ እንደሆነ ተመልክቷል።