ጥር 5 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የስዊዲን ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ከዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ኖርዌይ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራቅ እና ኢራን የመጡ በስዊድን የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሰልፉ ላይ ተገኝተዋል።
ሰልፈኞቹ የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ለህዝብ እንዲያሳውቅ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ስልጣን እንዲለቁ፣ የመለስ መንግስት ጋዜጠኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ እንዲሁም የስዊድን መንግስት ጋዜጠኞችን በገንዘብ ለማስፈታት የሚያደርገው ጥረት ባርነት በመሆኑ እንዲያቆም መጠየቁን ሙሉጌታ አበበ ከስዊድን ዘግቧል።
ኢትዮጵያውያን ሰልፈኞችም የመለስ መንግስት ስልጣን እንዲለቅ፣ ስዊድን ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን እርዳታ እንድታቋርጥ፣ የታሰሩት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የሰልፉ አስተባባሪ የሆኑት ዳኒ ሮስኪ ለኢሳት እንደገለጡት ሰልፉን ለማድረግ የተነሳሱት የቀድሞው ሉንዲን ኦይል ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና የአሁኑ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኦጋዴን ስለሚያከናውኑት ስራ እንዲገልጡ፣ ስልጣን በአስቸኳይ እንዲለቁ ለመጠየቅ ነው።
የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር አመራር አካል የሆኑት አቶ ሀሰን አብዱላሂ ለኢሳት እንደገለጡት በሰልፉ ላይ የተገኙት የመለስ መንግስት በሰራው ወንጀል ለፍርድ እንዲቀርብ፣ ሉንዲን ኦይል ለመለስ መንግስት የሚሰጠውን እርዳታ እንዲያቋርጥ ለመጠየቅ ነው።
አቶ ሀሰን የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይከፋፈል አንድ ላይ በመሆን ይህን የመለስን ዘረኛ መንግስትን ማስወገድ አለበት ብለዋል።