በአርባምንጭ ከተማ አንድ ለጸጥታ ስጋት ነው የተባለ የ18 ዓመት ወጣት በፖሊስ ጥይት ተበሳስቶ ተገደለ

ጥር 5 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-የኢሳት የአርባምንጭ ወኪል እንደገለጠው ወጣት ደግነት ጌታቸው ታህሳስ 28 ፣ 2004 ዓም ለገና በአል ዋዜማ ከጓደኞቹ ጋር ሲዝናና በነበረበት ወቅት፣ በፖሊሶች ተገድሏል።

ወጣት ደግነት  ለጸጥታ አደገኛ ነው በሚል ምክንያት ክትትል ሲደረግበት እንደነበር ዘጋቢያችን ገልጧል።

የወጣት ደግነት አባት የሆኑት አቶ ጌታቸው ለኢሳት እንደተናገሩት ልጃቸው የተገደለው ምንም ጥፋት ሳያጠፋ መሆኑን ገልጠው፣ ገዳይ ፖሊሶችን ለፍርድ ለማቅረብ አቅም ስለሌላቸው አዘናቸውን በቤታቸው አድርገው መቀመጣቸውን ተናግረዋል።

ልጃቸው ከተመታ በሁዋላ ህክምና መከልከሉንም አቶ ጌታቸው ይገልጣሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአርባምንጭ ወረዳ ባለስልጣን በርካታ የከተማው ወጣቶች ለጸጥታ ስጋት ናቸው እየተባሉ በመታሰር ላይ ናቸው ብለዋል።

ፖሊስም  ስጋት በተባሉ ወጣቶች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ሙሉ መብት ተሰጥቶታል ሲሉ አክለዋል።

በአርባምንጭ እና አካባቢዋ ከኑሮ ውድነት፣ ከመልካም አስተዳዳር እና ከፍትህ እጦት ጋር በተያያዘ በየጊዜው የተለያዩ ችግሮች  እንደሚከሰቱ ዘጋቢያችን አክሎ ገልጧል።