ጥር 3 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሰሞኑን ለቀምት ከተማ በሚገኘው የወለጋ ዩኒቨርስቲ ግጭት መፈጠሩን ተከትሎ ሲራጂ እና ከማል የተባሉ ሁለት የሕግ ተማሪዎች ሞቱ።
ተማሪዎቹ የተገደሉት በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት እስካሁን የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፤ ውስጥ አዋቂዎች ፦”ተማሪዎቹ የሞቱት በምግብ መመረዝ ነው”ማለታቸውን ፍኖተ -ነፃነት ዘግቧል።
የሟቾቹ ተማሪዎቹ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከትናንት በስቲያ ተፈጽሟል።
ስለጉዳዬ የ ዩኒቨርሲቲውን ሀላፊዎች ለማነጋገር የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት፤ሀላፊዎቹ ስልካቸውን ለማ ንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊሳካ አልቻለም።
ስሜ እንዲጠቀስ አልፈልግም ያሉ አንድ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባል ፦ “በእርግጥ ልጆቹ ሞተዋል፡፡ የሞቱት ግን በግጭቱ ሳይሆን “በምግብ መመረዝ ነው” በማለት ተማሪዎቹ በግጭቱ እንዳልተገደሉ አስተባብለዋል፡፡
ይሁንና ተማሪዎቹ የሞቱት በምግብ መመረዝም ሆነ በግጭት፤ መንግስትን ከተጠያቂነት እንደማያስመልጠው የህግ ባለሙያዎች አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል።
ሰሞኑን በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎችና በፌዴራል ፖሊሶች መካከል በተፈጠረ ግጭት የመማር ማስተማሩ ሂደት እንደተቋረጠ መዘገባችን ይታወሳል።