የኑሮ ውድነቱ ፤ ለእግር ኳስ ውድድር መቋረጥ ምክንያት ሆነ

ጥር 3 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-በቅዱስ ጊዮርጊስና በ አየር ሀይል ክለቦች መካከል ከትላንት በስቲያ በደብረዘይት ከተማ ሊከናወን የነበረው የእግር ኳስ ውድድር ፤ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ ተመልካቹ  ማሰማት በጀመረው ተቃውሞ መባባስ ምክንያት ተቋረጠ።

ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት በስቴዲዮሙ የተገኘው ተመልካች የወቅቱን የኑሮ ውድነትና  በገዥው ፓርቲ እየተፈጸመ ያለውን የአፈና ድርጊት በዜማና በግጥም  መቃወም መጀመሩን የዘገበው ፍኖተ-ነፃነት፤ በዚህ መልክ የተጀመረው የተመልካች ተቃውሞ ውድድሩም ከተጀመረ በኋላ ወደ ሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች መሸጋገሩን አመልክቷል።

ረብሻው እየጋለ ከመሄዱና ድብድብ ከመከሰቱ ባሻገር፤ በተመልካችና በፀጥታ አስከባሪዎች  መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ ወደ ተካረረ ሁኔታ በማምራቱና ሁኔታው መጥፎ አዝማሚያ በመያዙ ውድድሩ መቋረጡን የስታዲየሙ ታዳሚዎች ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለየ ሁኔታ በአዲስ አበባ ስታዲዮም በተጀመረው የአገዛዙን ድርጊቶች የመቃወም ልምድ ሳቢያ ፤የቅዱስ ጊዮርጊስና የቡና ስፖርት ክለቦች ለቅጣት መዳረጋቸው ይታወሳል።

የተወሰደባቸው እርምጃ ፦”አህያውን ፈርቶ ዳውላውን”መሆኑን የተገነዘቡት የሁለቱም ስፓርት ክለቦች፦”ቅጣቱ ፍትሀዊ አይደለም”በማለት መቃወማቸው አይዘነጋም።

“ህዝብ በተገኘውአጋጣሚ ሁሉ ከሚደርስበት አፈናና ግፍ ብሶቱን በማሰማቱ፤ ጉዳዩን ከማይመለከታቸው አካላት ጋር ከማገናኘት ይልቅ ህዝብን ማድመጥና መፍትሔ መፈለጉ ይሻላል” የጋዜጣው ምንጮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘንድሮ በተካሄደው  ታላቁ ሩጫ ህዝቡ ፦”እንደ ጋዳፊ መለስን በጥፊ!ሳንፈልጋቸው፤ሀያ ዓመታቸው”በማለት ተቃውሞውን መግለጹ ይታወቃል።