ጥር 2 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስ መንግስት ፤ ከጥር 1 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከ200 ሺ ብር ወይም ከ10 ሺ የአሜሪካን ዶላር በላይ ከባንክ የሚወጣ ወይም የሚገባ ገንዘብን አስመልክቶ ብሔራዊ ባንክ-ለፀረ-ሽብር ግብረ-ሀይል ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት የደነገገው አዲስ አዋጅ ተቃውሞና ትችት እየቀረበበት ነው።
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ በመጥቀስ ሰንደቅ እንደዘገበው፤ መመሪያው ሥራ ላይ የዋለው ኅብተሰቡን ስለ ጉዳዩ ግንዛቤና መረዳት ሳይኖረው በመሆኑ፤ በህዝቡ ዘንድ ፍርሀት ሊፈጥር ይችላል።
“ይህን መሰል የፋይናንስ ደህንነት የመረጃ ማዕከል ዓለም አቀፍ አሠራርን የተከተለ ቢሆንም፤ የዓለምን ኅብረተሰብ አንድ አይነት ሕዝብ አድርጐ መወሰን ግን አስቸጋሪ ነው”ያሉት የ ኢኮኖሚ ባለሙያው፤ “ለምሳሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ እና የአሜሪካን ሕዝብ በአንፃራዊነት ብንወስድ፤ በማኅበራዊ፣ በባህል፣ ገንዘብን በመጠቀምና በዳበረ እውቀት የተለያዩ ሆነው ነው የምናገኛቸው። ስለዚህም አንድ አዋጅ ወደ ተግባር ከመቀየሩ በፊት ኅብረተሰቡን በተገቢ ሁኔታ ማስተማር ያስፈልጋል። ማስተማርን ማስቀደም ኅብረተሰቡ ወደ ፍርሃት ውስጥ እንዳይገባ ያግዛል” ብለዋል።
አያይዘውም “በሀገራችን ነጋዴዎች ዘንድ ከግብር፣ ከባንክና ከኢንሹራንስ ጋር በተገናኘ መረጃን ለማሳወቅ ፍላጐቱም፤ ዝግጁነቱም የዳበረ አይደለም። ስለዚህም ይህ አዋጅ በከፍተኛ ትምህርት ካልታገዘ፤ በቀላሉ ወደ ኅብረተሰቡ ውስጥ ማስረፅ አዳጋች ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
በፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል፤ የፋይናንስ ግብይት ፍተሻና ትንተና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኪዳነማርያም ገ/ፃዲቅ ግን፦ “የእኛ ኅብረተሰብ ገቢ እና ወጪውን ለማሳወቅ ዝግጅት አይደለም የሚለው መከራከሪያ ብዙ አያስኬድም። ምክንያቱም በሀገራችን ያለው ነጋዴ የገንዘብ ገቢ እና ወጪውን ሪፖርት ከባንኮች በመውሰድ እየሰራ ይገኛል”ባይ ናቸው።
ዳይሬክተሩ አክለውም፦“ ከ200 ሺ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ሲወጣና ሲገባ ተመዝግቦ ይያዝ ነው የተባለው። ይህ ማለት ግን በጥሬ ገንዘብ ከ200 ሺ ብር በላይ ማስገባትና ማስወጣት በጥርጣሬ የሚታይ ወንጀል ነው የሚል አንዲትም ነገር የለም። በመረጃ ደረጃ ተመዝግቦ ይቀመጥ ብቻ ነው የተባለው። ለጥርጣሬ የሚያበቁ ነገሮች ራሳቸውን የቻሉ አተናተን ነው ያላቸው” ብለዋል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው ግን የዳይሬክተሩ ማብራሪያ እንዳልተዋጠላቸው ነው የሚናገሩት።
“ አፈፃፀሙ እንደመመሪያው የሚሆን አይመስለኝም ያሉት” የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ አዋጁ መውጣቱ ስጋትን ከመከላከል አንፃር ተገቢ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን (መኒ ላውንደሪግ) በተመለከተ ከኢራንና ከመሳሰሉ ሀገሮች ጋር እንደምትመደብ ነው የሚያመለክተው። ለዚህም ነው ተፈፃሚ አይሆንም የሚል አስተሳሰብ ያለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት ባንኮች የገንዘብ መጠኑ ምንም ያህል ቢሆን ጥርጣሬ ያለበት ገንዘብ ዝውውር ሲያጋጥም ቢበዛ በሦስት ቀናት ውስጥ “ጸረ-ሽብር ግብረ-ሀይል”ተብሎ ለሚጠራው ቡድን ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።
ግብረ-ሀይሉ ሪፖርት የተደረገለትን ገንዘብ አስመልክቶ መርምሮ የመወሰን ሙሉ ሀላፊነት ተሰጥቶታል።
“ ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ በወንጀል የተገኘን ገንዘብ- ወደ ኢኮኖሚ እንዲገባ ይቆጣጠራል”የሚል ሀላፊነትም ተረክቧል።