(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 14/2011)በአሜሪካን ኡበር የተሰኘ የታክሲ አገልግሎት ሹፌር በሶማሊያ የጦር ወንጀል በመፈጸሙ ለእስር ተዳረገ።
የቀድሞ የሶማሊያ መሪ የዚያድ ባሬ ወታደራዊ ኮማንደር ከ30ዓመታት በፊት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም በጦር ወንጀለኝነት የሚፈለግ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።
ትላንት በቨርጂኒያ አሌክሳንደሪያ የተሰየመው ችሎት ኮሎኔል ዩሱፍ ዓሊን ጥፋተኛ ብሎ ውሳኔ ሰጥቷል።
ኡበር የታክሲ አገልግሎትም ኮሎኔሉን ማባረሩን አስታውቋል።
በዚያድ ባሬ አገዛዝ ኮሎኔል የነበሩትና በአሜሪካን የኡበር ሹፌር በመሆን እየሰሩ የሚገኙት ዩሱፍ አብዲ ዓሊ ማሰቃየት በተፈጸመባቸው አንድ ሶማሊያዊ ክስ ከተመሰረባቸው በኋላ ለፍርድ ቀርበዋል።
ከሰላሳ ዓመት በፊት በእኚሁ ኮሎኔል በጥይት ተመተው ከፍተኛ ማሰቃየት የተፈጸመባቸው ፋራሃን ታኒ ዋርፋ ቨርጂኒያ አሌክሳንድሪያ ከተማ በተሰየመው ችሎት ቀርበው የደረሰባቸውን ጉዳት ምስክርነት በመስጠት ገልጸዋል።
ፋራሃን በቀድሞ ኮሎኔል ዩሱፍ አብዲ ታፍነው ከተወሰዱና በጥይትና በተለያዩ ማሰቃየቶች ከፍተኛ ድብደባ ከተፈጸመባቸው በኋላ ሞተዋል ተብለው እንደተጣሉ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።
እሳቸውን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሶማሌያውያን በኮሎኔል ዩስፍ አብዲ ስቃይ ተፈጽሞባቸዋል፡ በርካቶች ተገድለዋል።
የቀድሞ የዚያድ ባሬ ኮማንደር የአሁኑ የኡበር ታክሲ ሹፌር የሆኑት ኮሎኔል ዩሱፍ አብዲ ዓሊ ከሀገራቸው ካመለጡ በኋላ በካናዳ ይኖሩ እንደነበረ የፍርድ ቤት መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዚያድ ባሬን መንግስት ሸሽተው በካናዳ በጥገኝነት በሚኖሩ ሶማሊያውያን ጥቆማ በኮሎኔል ዩሱፍ ላይ የሚያጠነጥን ጥናታዊ ፊልም ለህዝብ መቅረቡን ተከትሎ ካናዳ ከሀገሯ ማባረሯም ታውቋል።
በኋላም አሜሪካ ገብተው መኖር የጀመሩት ኮሎኔል ዩሱፍ በ1996 እንደአውሮፖያኑ አቆጣጠር በአሜሪካን መንግስት ከሃገር እንዲወጡ መደረጉንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁንና ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ ኮሎኔል ዩሱፍ አሜሪካን በድጋሚ መግባታቸው ነው በፍርድ ቤት የቀረበው ማስረጃ ላይ የተመለከተው።
በጦር ወንጀል የሚፈለጉትን ሶማሊያዊ ኮሎኔል በድጋሚ አሜሪካ መግባቱ የአሜሪካንን የደህንነትና የስለላ መስሪያ ቤቶችን እያወዛገበ ነው።
የአሜሪካን የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ትላንት በአሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ የተሰየመው ችሎት ኮሎኔል ዩሱፍ አብዲን ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
በችሎቱ ተገኝተው ምስክርነት የሰጡት ፋራሃን ለደረሰባቸው ጉዳት የ500ሺህ ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸውም ፍርድ ቤቱ አዟል።
ፋራሃን በመጨረሻም ወንጀለኛ ከፍትህ እንደማያመልጥ ያረጋገጠ የፍርድ ሂደት በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የ31 ዓመት የፍትህ ጥያቄ መልስ ያገኘበትም ብለዋል ፋራሃን። ከእሳቸው ጋር የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደር፣ በኮሎኔል ዩሱፍ ስር የነበሩ ሶማሊያውያን ወታደሮችና ሌሎች ግለሰቦች ምስክርነት ሰጥተዋል።
ኮሎኔል ዓሊ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሶማሊያውያን ላይ ከፍተኛ ማሰቃየት ፈጽመዋል በሚል ውሳኔ የሰጠው የአሌክሳንደሪያ ፍርድ ቤት አሜሪካን የወንጀለንኞች መደበቂያ እንደማትሆን ያረጋገጠ ትልቅ የፍትህ ድል ነው ሲሉ የፋራሃን ጠበቃ ተናግረዋል።
በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ላለፉት 18 ወራት በኡበር ታክሲ ስራ የቆዩት ኮሎኔል ዩሱፍ አብዲ ዓሊ ቀደም ብለው በዋሽንግተን ዳላስ አውሮፕላን ማረፊያ የደህንነት ሰራተኛ ሆነው መስራታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ኡበር የታክሲ አገልግሎት ኮሎኔል ዩሱፍን ከስራው ሙሉ በሙሉ ማገዱን አስታውቋል።