ጥር 1 ቀን 2004 ዓም
ኢሳት ዜና:-የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ለዛሬ ለፍርድ ቀጥሮት የነበረውን በእነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ በአሸባሪነት ወንጀል የተከሰሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባልና ጋዜጠኞች ላይ ከጥፋት ነፃ ናቸው አሊያም ጥፋተኛ ናቸው የሚል ፍርድ ዛሬ ሳይሰጥ ቀረ፡፡
የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ በአሸባሪነት ወንጀል ክስ የመሠረተባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚያብሄር፣ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ ርዮት ዓለሙ እና ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ ለፍርድ የቀረቡ ቢሆንም ፍርድ ባለማግኘታቸው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በአጀንዳው ላይ ”ፍርድ የእግዚሃብሄር ነው‘ የሚል በትልቁ ጽፎ ለጋዜጠኞች አስነብቧል፡፡
የመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ፣ የቀኝ ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ እና የግራ ዳኛ በሪሁን አራጋው ባስቻሉት ችሎት ላይ በመሐል ዳኛው ንባብ እንደቀረበው መዝገቡ ለፍርድ ተቀጥሮ እንደነበር፣ ነገር ግን ታህሳስ 11 ቀን 2004 ዓ.ም በካሴት የተቀረጸው የተከሳሽ ምስክሮች ቃል ወደ ጽሑፍ ተገልብጦ ለፍርድ ቤቱ እንዳልደረሰው በመግለጽ በተከሳሾች ላይ ፍርድ ለመስጠት መቸገራቸውን አሳውቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በእለቱ ባስተላለፈው ትዕዛዝ ፍርድ ለመስጠት ለጥር 10 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን ከዕለቱ ቀደም ብሎ ካሴቱ ወደ ጽሑፍ ተቀይሮ እንዲቀርብለት ያዘዘ ሲሆን እስካሁን የዘገየበትንም ምክንያት ቀርበው እንዲያስረዱ ውሳኔ አስተላልፎ ችሎቱ ተበትኗል፡፡
ከችሎት ውጪ ሪፖርተራችን ያናገራቸው አንድ የህግ ሰው እንግዲህ የፍርድ ትዕዛዝ ከላይ ከመንግስት ስላልወረደላቸው ነው ጊዜ ማግኛ ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ የሰጡት፣ ያውም በጥምቀት በዓል ላይ እንዲሆን ቀኑን ሆን ብለው አርቀው ገፍተውታል ብለዋል፡፡
ተከሳሾቹ በ6 ክልሎች በሚገኙ የስልክና የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ጉዳት በማድረስና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ፈጽመዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የውጭ አገር መንግስታትና ድርጅቶች እንዲሁም አብዛኛው ህዝብ ክሱ የፈጠራና የፖለቲካ ስልጣንን ለማራዘም ተብሎ የተቀነባበረ ነው ብሎ ያምናል።