አዴሃን የአማራ ክልል መንግስት ቃሉን አልጠበቀም በሚል የተቃውሞ ሰልፍ አደረገ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 2/2011) የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ አዴሃን የአማራ ክልል መንግስት ቃሉን አልጠበቀም በሚል በዛሬው ዕለት የተቃውሞ ሰልፍ አደረገ።

ከስምንት ወራት በፊት ከኤርትራ ትጥቁን በመፍታት ወደሃገር ቤት የገባው አዴሃን ከክልሉ ገዢ ፓርቲ አዴፓ ጋር ከደረሳቸው ባለ 41ነጥብ ስምምነቶች አንዳቸውም ተግባራዊ አልተደረጉም ሲል አስታውቋል።

የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህ ለኢሳት እንደገለጹት የአዴሃን አባላት በከፋ ችግር እየተሰቃዩ ናቸው።

በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከምርጫ ቦርድ ሰርተፍኬት አግኝቼ እየተንቀሳቀስኩ ነው የሚለው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ አዴሃን በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን መፈናቀል ለማስቆም በክልሉ መንግስት በኩል የሚደረገው ጥረት በቂ አይደለም ሲል ተቃውሞውን አቅርቧል።

ዛሬ በባህርዳር ከተማ በአዴሃን ለተደረገው ሰልፍ በክልሉ መንግስት በኩል ታገሱን ከሚል ውጭ የተሰጠ ምላሽ እንደሌለ የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ ለኢሳት ገልጸዋል።